በኢትዮጵያ የሣንሱር ሥጋት እያወዛገበ ነው

የመንግሥት ማተሚያ ድርጅቶች ያዘጋጁት የሕትመት ሥራ ውል “በሕግ ዕገዳ የተጣለበትን ቅድሚያ ምርመራን ይተገብራል” ያሉ የብዙ ጋዜጦች አሣታሚዎች ውሉን ከመፈረም ጋዜጦቻቸውን መዝጋት እንደሚቀልላቸው ይናገራሉ፡፡

በብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት የተዘጋጀው ረቂቅ ርዕሱ “የሕትመት ሥራ ስታንዳርድ ውል” የሚል ነው፡፡ ረቂቱ 11 አንቀፆች ያሉት ሲሆን የውሉ ዓላማ በአጭሩ አሣታሚው ለአታሚው በሚሰጠው የሥራ ትዕዛዝ መሠረት አትሞ ለማስረከብ የሚያስችል ቋሚ የስምነት ሠነድ ለመፍጠር ነው፡፡

ከ14 የማያንሱ ጋዜጦች አሣታሚዎች ግን ይህንን ውል “አንፈርምም” ብለዋል፡፡ በረቂቁ ውል ላይ ከአታሚው ድርጅት ጋር እንዲነጋገሩ አራት አሣታሚዎች ተወክለዋል፡፡

በውሉ አንቀፅ አሥር ሥር አንቀፅ 10.1 እና 10.2 ወይም 10.ሀ እና 10.ለ በሕገመንግሥቱ የተረጋገጠውን የዜጎች መሠረታዊ መብት፤ የመናገር ነፃነት፣ ሃሣብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ ተመሥርተው የሚመሩበትን የፕሬስ ነፃነት የሚቃረን፣ በሕገመንግሥቱ እና በመገናኛ ብዙኃን ሕጉ በግልፅ ዕገዳ የተጣለበትን የቅድሚያ ምርመራ ወይም ሳንሱር ሊተገብር የሚያስችል አቅም ያለው አስተሣሰብ ያለው መሆኑን የሚገልፁት እነዚሁ አሣታሚዎች ውሉን እንደሚቃወሙ አሣታሚዎቹን ወክሎ ከቪኦኤ ጋር ቃለምልልስ ያደረገው የፎርቹን ጋዜጣ አሣታሚና ማኔጂንግ ኤዲተር ታምራት ገብረጊዮርጊስ አመልክቷል፡፡

ዝርዝሩን ከዘገባው ያዳምጡ፡፡