ኢትዮጵያ አዲስ  ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሾመች 

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ

Your browser doesn’t support HTML5

ኢትዮጵያ አዲስ  ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሾመች 

ዛሬ ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ/ም የካቢኔ ሹመቶችን ይፋ ያደረጉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የፍትሕ ሚኒስትር የነበሩትን ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው ሾሙ። ዶ/ር ጌዲዮን፣በቅርቡ በፕሬዝደንትነት የተሾሙትን አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴን ይተካሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሎች ሁለት የሚኒስትርነት ሹመቶችንም መስጠታቸውን ጽሕፈት ቤታቸው አስታውቋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ያስታወቀው ዛሬ አርብ ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው መረጃ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ መምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩበት የዶ/ር ጌዲዮን የመንግሥት ኃላፊነት ዘመን የጀመረው በጥቅምት ወር 2011 ዓ/ም በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆነው ሲሾሙ ነበር።

ከነሐሴ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመሆን አገልግለዋል። ከአንድ ዓመት በኋላ መስሪያ ቤቱ ወደ ፍትሕ ሚኒስቴርነት ሲቀየር የፍትሕ ሚኒስትር ሆነው የተሸሙት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስከሆኑበት እስከ ዛሬው ቀን ድረስም በዚሁ ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በተደረገው የፕሪቶሪያው የሰላም ድርድር ላይ፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ከወከሉ ተደራዳሪዎች መካከል ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ አንዱ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ሹመት፣ ከዶ/ር ጌዲዮን በተጨማሪ ሌሎች ሁለት አዳዲስ ሚኒስትሮችን ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር የነበሩት ወ/ሮ ሃና አርአያ ሥላሴ በጌዲዮን ምትክ የፍትሕ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

አዲሷ የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርአያ ሥላሴ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነውም ሰርተዋል፡፡

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩት ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። አዲሷ ሚኒስትር እስከ ዛሬ ድረስ የቱሪዝም ሚኒስትር የነበሩትን አምባሳደር ናሲሴ ጫሊን ይተካሉ።

ወ/ሮ ሰላማዊት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በጋዜጠኝነትም ሠርተዋል፡፡