ዋና ከተማዋን ዐዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች፤ ከዛሬ ማክሰኞ ከሰዓት ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ ውሏል።
ዐዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የአሜሪካ ድምጽ ዘጋቢዎች፣ በሚገኙባቸው ከተሞችና በዙሪያቸው የኤሌትሪክ ኃይል መቋረጡን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በፈስቡክ ገጹ ባሰፈረው መግለጫ፤ በጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ ባጋጠመ የቴክኒክ ችግር ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች የኃይል መቋረጥ ማጋጠሙን አስታውቋል፡፡
በኃይል ማመንጫ ጣቢያው ላይ ያጋጠመውን የቴክኒክ ችግር ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጿል።
ከዚሁ ጋራ ተያይዞ በአዲስ አበባ ተቋርጦ የነበረው ኤሌክትሪክ አገልግሎት ወደ ነበረበት መመለሱን ተቋሙ ማምሻውን ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አስታውቋል።
በተቀሩት የሀገሪቱ ክፍሎች ያጋጠመውን የኤሌክትሪክ መቋረጥ ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አመልክቷል። የዛሬው ሰፋ ያለ ይሁን እንጅ በተለይ ከክረምቱ ወቅት መግባት በኋላ ከፍተኛ የኃይል መቆራረጥ እያጋጠመ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።