በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማለቁን ተከትሎ፣ ሁለት የክልሉ ባለሥልታናት መገደላቸውን የአካባቢ አስተዳደሮች አስታውቀዋል።
የኤፍራታ ግድም እና የቀወት ወረዳ አስተዳዳሪዎች “አክራሪ ቡድኖች” ብለው በገለጿቸው አካላት ባለፈው እሁድ ግንቦት 25 እና ረቡዕ ግንቦት 5፣ 2016 ዓ/ም እንደተገደሉ አስተዳደሮቹ በተናጥል ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። በተለምዶ መንግሥት “አክራሪ ቡድን” ብሎ የሚገልፃቸው በክልልሉ የሚገኙ የፋኖ ሚሊሺያዎችን እንደሆነ የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።
ባለፈው የካቲት ተራዝሞ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው ሳምንት ቢያበቃም፣ መንግሥት የአዋጁን መነሳት በይፋ አላሳወቀም። አዋጁን ለማስቀጠል መንግስት እስከ አለፈው ማክሠኞ ድረስ በፓርላማ ማስጸደቅ ቢጠበቅበትም ያንን ሲያደርግ አልተስተዋለም።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ የታሰሩ ሰዎች እንዲለቀቁ እና ሕግ እንዲከበር ጠይቋል።
በሃገሪቱ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ በሆነውና 23 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርበት የአማራ ክልል የፋኖ ሚሊሻዎች ያስነሱትን አመፅ መንግስት ማቆም እንዳልቻለ የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።
በሱዳን የሚካሄደውን ጦርነት በመሸሽ አማራ ክልል የገቡ ፍልሰተኞችም በአካባቢው የሚታየው ውጥረት እንዲባባስ ማድረጋቸው ተመልክቷል።
ባለፈው ወር 1ሺሕ የሚሆኑ ፍልሰተኞች ዘረፋ፣ ተኩስ እና ጠለፋ ይደርስብናል በማለት መጠለያቸውን ጥለው እንደወጡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቆ ነበር።