አቶ ኪሮስ ዳኘው የተባሉ ባለሃብት ከእሥራኤል እጅግ ዘመናዊ የተባለ መሣሪያ አስመጥተው ነው እርሻውን የጀመሩት፡፡ ይህ እርሻ በስፋት የሚያመርተው ፍራፍሬ ሲሆን ለሥራው እገዛ የሚያደርጉ ባለሙያዎችንም አስመጥተዋል፡፡
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ እንግዳ ኪሮስ ስለእርሻው ዘመናዊነት ሲናገሩ በኮምፕዩተር የሚታገዘውን ይህንን እርሻ ለመጠጣት 180 ሜትር ጥልቀት ካለው ጉድጓድ ውኃ እንደሚስቡና ማዳበሪያና ውኃውን ቀላቅሎ የሚሰጥ መሣሪያም መትከላቸውን አመልክተዋል፡፡
ሁሉም ሥራ በኮምፕዩተር የሚታዘዝ በመሆኑ ከሃገር ውጭ እንኳ ሆነው በኢንተርኔት እየተከታተሉ እርሻቸውን እንደሚመሩ አቶ እንግዳ ገልፀዋል፡፡
ዛሬ እሥራኤል ውስጥ የሚሠራበትን እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይዘው ሥራውን የጀመሩት ከአማራ ክልል ተጋብዘው መሆኑን የሚናገሩት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ብዙ ችግር እንዳልገጠማቸው ቢገልፁም በወረዳ ደረጃ ያለው ሥልጣን እነርሱ ከሚፈልጓቸው አገልግሎቶች ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከእሥራኤል ነታፊም ከተባለው ድርጅት የመጡት የአትክልትና ፍራፍሬ ከፍተኛ ባለሙያ ኤሊ ማታን ኢትዮጵያዊያኑ የጀመሩትን ዘመናዊ የእርሻ ዘዴ እንደሚያደንቁ ተናግረዋል፡፡
"በመጀመሪያ በኢትዮጵያ የነበረውን ልማዳዊ የእርሻ ዘዴ በማስቀረት ዘመናዊውን የእርሻ ዘዴ የሚከተሉ ሰዎችን ማየቴ በጣም አስደስቶኛል፡፡" ብለዋል ሚስተር ማታን፡፡
በዚህ የእርሻ ቦታ ላይ የሚገኙ ሰዎች በጣም ዘመናዊ የተባለ መሣሪያ ማግኘታቸውን የሚገልፁት ማታን ይሁን እንጂ ከፍተኛ የሙያ ማነስ ችግር እንደሚታይም ይናገራሉ፡፡ "ድርጅታችን በደንበኞቻችን ላይ የሚታየውን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት የተቻለውን ያህል በመጣር ላይ ነው፡፡" ብለዋል ባለሙያው ኤሊ ማታን፡፡
"ሁልጊዜ ባለሙያ ከእሥራኤል ማስመጣት አይቻልም፡፡" የሚሉት ማታን የተሻለው መፍትሔ የሚሆነው በአካባቢው የሚገኙ የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያዎችን በዘመናዊ የእርሻ አመራር ማሠልጠን እንደሆነ ይመክራሉ፡፡
ዝርዝሩን ከዘገባው ያዳምጡ፡፡