የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሐሙስ ሚያዚያ 26 ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ምርጫ ቦርድ የፓርቲአችንን ሕልውና የሚያጠፋ እርምጃ እየወሰደ ነው ብሏል።
ድርጅቱ ለክሡ መነሻ ያደረገው ምርጫ ቦርድ መጋቢት 17/2004 ዓ.ም በፃፈለት ደብዳቤ የፓርቲው ማኅተም ሊያገለግል የሚችለው እስከ ሚያዝያ 30/2004 ዓም ብቻ መሆኑን ማስታወቁን ነው።
ቦርዱ ለዚህ የሰጠው ምክንያት “በፓርቲው አመራር አባላት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በጠቅላላ ጉባዔ እንዲፈታ በማሰብ” መሆኑን ይገልፃል። ከዚህ በፊትም ማኅተሙ የሚያገለግለው እስከ ሚያዝያ 30 ብቻ መሆኑን እንደገለፀም አስታውሷል።
የመኢአድ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ወንድማገኝ ደነቀ ግን ካሁን ቀደም እስከ ታህሳሥ 30 የማኅተሙን ጉዳይ ጨምሮ የሚነጋገር ጠቅላላ ጉባዔ ጥሩ የሚል ደብዳቤ ተልኮላቸው እንደነበር ተናግረዋል።
“በአዋጁና በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ግን ጠቅላላ ጉባዔ የሚጠራው በሁለት ዓመት አንዴ በመሆኑ እኛ ገና አንድ ዓመት ብቻ ሰለሆነን ጠቅላላ ጉባዔ መጥራት አንችልም የሚል መልስ ሰጥተን ነበር፤ ከምርጫ ቦርድ ግን የተሰጠን መልስ የለም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ ወይዘሮ የሺ ፈቃደ ግን “በመኢአድ ህገ-ደንብ ላይ እንደተመለከተው አመራርና ሥራ አስፈፃሚዎችን ማባረር የሚችለው ጠቅላላ ጉባዔው ነው፤ እኛ እየጠየቅን ያለነው ፓርቲው የራሱን ሕገ-ደንብ ተግባራዊ እንዲያደርግ ነው” ብለዋል።
ዝርዝሩን ከእስክንድር ፍሬዉ ዘገባ ያድምጡ