ባለፈው የዝናብ ወቅት በኢትዮጵያ አብዛኞቹ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሚባል የዝናብ መጠን መጣሉ ተገልጿል፡፡
የድርቁ ሁኔታ በበረታባቸው የምሥራቅና የደቡብ ምሥራቅ አባባቢዎች መጠነኛም ቢሆን ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ምክትል ምና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዱላ ሻንቆ አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ክረምት ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ከሰኔ እስከመስከረም ባለው ጊዜ ከጥቂት የሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች በስተቀር ዝናብ ማግኘት ያለባቸው አካባቢዎች በጥሩ ሁኔታ ማግኘታቸውን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡
በእነዚያ የሰሜን ምዕራብ አካባቢዎችም ቢሆን የዝናቡ መጠን ከወትሮው ያነሰ ከመሆኑ በስተቀር ለድርቅ ያጋለጠ ሁኔታ አለመኖሩንና ለሰብሉም በቂ ዝናብ መጣሉን አመልክተዋል፡፡
በአንዳንድ የሰሜን ኢትዮጵያና የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ደግሞ በሰኔ መጨረሻና ሐምሌ መጀመሪያ አካባበ የዝናብ መቋረጥ እንደነበረና ክረምቱ ዘግይቶ መግባቱን፣ በዚህም ምክንያት በርከት ያሉ ደረቅ ቀናት እንደነበሩ አቶ ዱላ ገልፀዋል፡፡
በአፋር ሚሌ አካባቢና በጋምቤላ ወንዞች ሞልተው መፍሰሳቸውን ጠቁመው የደረሰ ጉዳት ግን እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡
ዝርዝሩን ከቃለምልልሱ ያዳምጡ፡፡