የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጉብኝት በሱዳን

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ጄኔራል አብድል ፈታ ቡርሃን

የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሱዳን የሚያደርጉትን ጉብኘት በዛሬው እለትም ቀጥለዋል፡፡ የሱዳን ባለሥልጣናት ኢሳያስ ከገዢው የሱዳን የልእልና ምክር ቤት መሪ ከጄኔራል አብድል ፈታ ቡርሃን ጋር በሁለቱ አገራት የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ እየተነጋገሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የሆነው ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳዮች ላይ ያላቸው አለመግባባት በተከሰተበትና ኤርትራም የትግራይን ግጭት አስመልከቶ ኢትዮጵያን ትደግፋለች የሚል ክስ እየተሰነዘረባት ባለበት ወቅት ነው፡፡

በዚህ ዙሪያ ኒዮርክ ውስጥ በሚገኘው የሎንግ አይላንድ ዩኒቨርስቲ፣ የቢዝነስ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑትን የሱዳን ተወላጅ ባክሪ ኤልመድኒን፣ የቪኦኤ ዘጋቢ ጀምስ ባቲ አነጋግሯቸዋል፡፡

የሱዳን ተወላጅ የሆኑት ባክሪ ኤልመድኒ ኒዮክር በሚገኘ የሎንግ አይላንድ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ኤርትራ እንደ አንድ ትንሽ አገር ከኢትዮጵያና ከሱዳን አንዳቸውን መምረጥ አትፈልግም፡፡ ስለሆነም የፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሱዳን ጉበኝት ዓላማም ይኸው ይመስለኛል ይላሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ኤርትራ በሁለቱ ትላልቅ አጎራባች አገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ማስወገድ ትፈልጋለች፡፡

ምክንያቱንም እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡፡

“ምክንያቱም በክልሉ እየሆነ ያለው በቀጠናው ከተፈጠረው አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በድንበሩም ሆነ በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረውም ያለመግባባት ሁኔታ ከዚህ ጋር ያያዛል፡፡ ስለዚህ ኢሳያስ ደግሞ ሁሌም በአካባቢው የተፈጠሩትን ሁኔታዎችን እያዩ ከሳቸው አገር በላይ ከተለቀ አገርም ጋር ይሁን ከሌላ ራሳቸውን ተፈላጊ ሰው አድርገው ማቅረብ የሚችሉ ሰው ናቸው፡፡”

በሱዳን ያደረጉት ጉብኝታቸው ዋና ዓላማ ታዲያ ምን ይመስልዎታል? ተብለው የተጠየቁት ኤልመድኒ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

“ለዚህ ጉብኝት ሁለት ምክንያቶች ያሉት ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ኢሳያስ ከሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል ከሁለት አንዱን ለመምረጥ በሚገደዱበት አጣብቂኝ ውስጥ መግባት አይፈልጉም በብዙ ምክንያቶች፡፡ ሱዳን ያልተረጋጋች አገር ናት፡፡ የኤርትራንም ደህንነት ራሱ ለማናጋት የምትችል አገር ልትሆን ትችላለች፡፡ በሌላ በኩልም እንዲሁ ኢሳያስ ለኢትዮጵያውያን ራሳቸው ቀላል ያልሆነውን ውብስብ ችግር ለመፍታት እንደሚችሉ አድርገው ነው የሚያዩት፡፡ ስለዚህ እንደሚመስለኝ ኢሳያስ ድምጻቸውን አጥፍተው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ችግር ለመፍታትና ከኢትዮጵያም ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለመጠበቅና ሰላም ለማስፈን የሚሞክሩ ይመስላሉ፡፡”

Your browser doesn’t support HTML5

የኤትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጉብኝት በሱዳን

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ወደ ሱዳን ባመሩበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በትግራይ ክልል ያለው ችግር አለ፡፡ ኤርትራም በትግራዩ ግጭት ጣልቃ በመግባቷ እየተከሰሰች ነው፡፡ ሱዳንና ኢትዮጵያም በመካከላቸው የመሬት ይገባኛል ክርክር አለ፡፡ ስለዚህ የኤርትራ መሪ በሁሉቱ አገሮች መካከል የአስታራቂነት ሚና እየተጫወቱ ይሆን የሚል ጥያቄም ለሱዳናዊው ፕሮፈሰር ኤልመድኒ ቀርቦላቸዋል፡፡ እንዲህ ብለው መለሱ

“አይመስለኝም፡፡ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ችግር ብዙ ዘርፎች ያሉትና በጣም የተወሳሰበ ነው፡፡ ኤርትራ በዚህ ሰዓት ምንም የስትራቴጂ አቅም የላትም፡፡ ኤርትራ በጣም ትንሽ አገር ናት፡፡ በርግጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአንጻራዊነት ሲታይ የተረጋጋች አገር ናት፡፡ ይሁን እንጂ ስትራጂክ ጠቀሜታን በሚመለከት ልትሰጠው የምትችለው ምንም ነገር የላትም፡፡ ኢሳያስ ማድረግ የሚፈልጉት ግን ያንን ይመስለኛል፡፡ ራሳቸውን ትልቅ አድርገው የኢሳያስ ጥሩ ወዳጅና አጋር እንዲሁም ለሱዳን ከማንም በላይ የሚቀርቡ፣ ከወጣትነታቸው ጀምረው ብዙዎቹ ታጋዮች በሱዳን የኖሩ በመሆናቸው የሱዳንን ባህል የሚያውቁና የሚጋሩ መሆናቸውን ማሳየት ይፈልጋሉ፡፡ ያንን ሚና መጫወት እንደሚፈልጉ መገመት እችላለሁ፡፡ ጥያቄው ግን ለዚያ ብቁ የሚሆኑን እንኳ ቢሆኑ ሊያመጡ የሚችሉት ጥሩ ነገር ይኖራል? እኔ አይመስለኝም፡፡”

ከቀደሞ የሱዳን አልበሽር ጋር ወዳጅ የነበሩና በሳቸውም መንግሥት ያገለገሉ አንድ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣን በፕሬዛዳንቱ ላይና በሳቸው ላይ የተመስረተውን የዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ክስ በሚያየው ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ፈቃደኛ መሆናቸውም የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

ባለሥልጣኑ አሁን ያለው የሱዳን የሽግግር መንግሥት ደካማና ያልተሳካለት መንግሥት መሆኑን ገልጸው “ይህ መንግሥት የወደቀ ስለሆነ ፍትህን ማስፈን የሚችል አይመስለመኝም” በማለት ወደ ሄግ አምርተው በፍርድ ቤቱ ፊት መቆም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

“ይሄ ለፖለቲካ ፍጆታ የተደረገ እንጂ ከልብ የመነጨ አይመስለኝም፡” ያሉት ፕሮፌሰር አልመድኒ፡፡ “ምናልባት ባለሥልጣኑ እውነታቸውን ሊሆን ይችላል፡፡ እውነት ነው ሱዳን ውስጥ ችግር አለ፣ መንግሥቱ በጣም ደካማ ነው፡፡ ብዙ ያልታወቁ ነገሮች አሉ፡፡ ምናልባት አንድ ቦታም ላይ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡” ብለዋል፡፡

“ይሁን እንጂ” አሉ ፕሮፌሰሩ “በጦር ወንጀለኝነት የሚፈለጉት እኚህ የአልበሽር ዘመን ባለሥልጣን ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት መሄዱን አይጠሉትም ምክንያቱም በፍርድ ቤቱ መርህ እዚያ የሞት ቅጣት የለም፡፡ ጥፋተኛ ከተባሉ ግፋ ቢል 10 እና 15 ዓመት ዓመት ቢፈረድባቸው ነው፡፡

በሱዳን የሆነ እንደሆነ ግን ጥፋተኛ ከተባሉ የሞት ፍርድ ሊጠብቃቸው ይችላልና ብለዋል፡፡