ለአውሮፓ ኅብረት የኤርትራ መልስ

  • ቪኦኤ ዜና
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል

“የኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉትን ቀውሶች በሚመለከት የችግሮቹን መሠረት የሸፋፈነ መግለጫ የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ተጠሪዎች ማውጣታቸው እጅግ አሳዛኝ ነው” ሲሉ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ወቅሰዋል።

“የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በትዊተር ገፃቸው ባሠፈሩት ፅሁፍ የአውሮፓ ኅብረት ወደ ክልሉ ሃቅ የሚያጣራ የልዑካን ቡድን ለማሠማራት ዕቅድ ይዞ በዋዜማው ይህን መግለጫ ማውጣቱ የሚያጠያይቅም ግራ የሚያጋባም ነው” ብለዋል።

አስከትለውም “የአውሮፓ ኅብረት የተወገደው የህወሓት ቡድን በሃገሪቱ በአሥሮች ዓመታት ለሚቆጠር ጊዜ ይዞት ከቆየው የጎሣ ልዩነትንና መከፋፈልን ተቋማዊ ካደረገ መርዘኛ ፖሊሲና ያልተገታ ሁከትና ትርምስ ጋር ተስማምቶ ያንን ወደጎን በመተው ‘በሀገሪቱ ሁከት እየተባባሰ” መሆኑን በማጉላት ይጮኻል” ሲሉ አቶ የማነ ነቅፈዋል።

“ኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪካዊ የሰላም ስምምነታቸውን አሥመራ ላይ ከተፈራረሙ በኋላም የህወሓት ቡድን ዓለምአቀፍ ህግጋትና በአውሮፓ ኅብረትና በሌሎችም ኃያላን ሽምግልና የተደረሰውን የአልጄርሱን ስምምነት በመጣስ የኤርትራን ሉዓላዊ ግዛቶች ይዞ ቆይቷል” ሲሉም አቶ የማነ አክለዋል።

“በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ የአውሮፓ ኅብረት ያለበትን የሞራል ግዴታ ቸል ብሎ ለቡድኑ በብዙ ቢሊዮን የተቆጠረ የበጀት እና ሌላም ድጋፍ መስጠቱን በመቀጠል ቡድኑ የጥፋት አድራጎቶቹን እንዲገፋ እየተበረታታ እንዲሄድ አድርጓል” ያሉት የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር “ኅብረቱ ኤርትራን መወንጀሉን ትቶ የራሱን ፖሊሲ እንደገና ይፈትሽ” ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስነብበዋል።