ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት እኤአ ካለፈው መጋቢት 2017 ወዲህ ከአስራ አምስት ሺህ በላይ ኤርትራውያን ሥደተኞችን ተቀብሎ ትግራይ ክልል ውስጥ ማስፈሩን አስታወቀ።
ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግሥት የሥደተኞችና ከሥደት ተመላሶች አስተዳደር እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን /ዩኤንኤችሲአር/ ጋር በቅርበት በመተባበር አዲስ ገቢ ኤርትራውያን ሥደተኞችን ኢንዳባጉና ከሚገኘው የሥደተኛ መቀበያ ማዕከል በክልሉ ወደሚገኙ አራት የሥደተኛ ካምፖች አጓጉዘዋል።
ትግራይ ክልል ሽሬ የሚገኘው የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ቢሮ ኃላፊ ሐታብ ኻሊድ በሰጡት ቃል በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ አንድ መቶ ሰዎችን ተቀብለን በማስፈር ላይ ነን ብለው የሚገቡት ሥደተኞች ቁጥር በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት መጨመሩን እንደሚጠቁም ገልጸዋል ።
በወጡ ኦፊሴላዊ አሃዞች መሰረት ባለፈው የአውሮፓውያን 2016 ኢትዮጵያ የገቡ ኤርትራውያን ሥደተኞች ቁጥር ሃያ አንድ ሺህ ሁለት መቶ አሥራ አምሥት ሲሆን እአአ 2017 ደግሞ እስካሁን በአለው ጊዜ የገቡት ቁጥር ከሃያ ሺህ መብለጡን ይጠቁማል። አብዛኞቹ ሥደተኞች ወጣቶች መሆናቸውንና /አይኦኤም/ ካሰፈራቸው መካከል አርባ ስድስት ከመቶው ከአሥራ ሥምንት እስከ ሃያ አራት ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል።