“የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን የለቀቀ ቢሆንም በእሥር ላይ በሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ዋና ፀሐፊ አቶ በቀለ ገርባ ላይ አንድ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ችሎት በመዳፈር የስድሥት ወር ተጨማሪ እስራት መወሰኑ በጥልቅ አሳስቦናል” ሲሉ በዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ አንጋፋ አባል ኢሊየት ኤንግል ገለፁ።
ዋሺንግተን ዲሲ —

ዲሞክራቱ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ኢሊየት ኤንግል ትናንት ባወጡት መግለጫ “የተወካዮች ምክር ቤቱ የሁለቱንም ፓርቲዎች አባላት የሚቅፈው ቶም ላንቶስ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የኅሊና እሥረኛ ናቸው ሲል የገለፃቸው አቶ በቀለ ገርባ ህመም ላይ መሆናቸውን ተረድተናል” ብለዋል።
እንደራሴ ኢንግል አያይዘውም ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ጋር በምታደርገው ግንኙነት አቶ በቀለ ገርባን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪዎች ደኅንነት ቅድሚያ ትኩረት ልትሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።
“ስለዚህም በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ እና አሣታፊ መንግሥት እንዲኖር የሚጠይቀውን ውሳኔ ቁጥር 128ን ካዘጋጁትና ካቀረቡት ሰዎች አንዱ በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል ኤንግል።