ደመወዝ መክፈል ግዴታ ነው - ኢሰመኮ/አይኤልኦ

Your browser doesn’t support HTML5

ደመወዝ መክፈል ግዴታ ነው - ኢሰመኮ/አይኤልኦ

የአራት ወራት ደመወዝ እንዳልተከፈለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከትናንት በስቲያ (ዕሁድ) ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

ሠራተኞቹ ለበረታ ቀውስ መዳረጋቸውን የኮሚሽኑ የማኅበራዊና ኢኮኖሚ መብቶች ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከጥቅምት 21 እስከ ኅዳር 4 / 2016 ዓ.ም. ሾኔና ሆሳዕና ከተሞች፣ ምሥራቅና ምዕራብ ባድዋቾ፣ እንዲሁም ጎምቦራ ወረዳዎች፣ ተገኝቶ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉ ነዋሪዎችንና የመንግሥት ተጠሪዎችን ማነጋገሩን ገልጿል።

በጤናና በትምህርት፣ እንዲሁም በሌሎችም ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት ተቋማት ላይ ቅኝት በማድረግ ምርመራ ማድረጉን የኮሚሽኑ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከፖሊስ፣ ከፍርድ ቤቶች እና ከፍትሕ ፅህፈት ቤት ሠራተኞች በስተቀር በአብዛኛው የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ከነኀሴ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ምርመራው እስከተከናወነበት ያለፈው ወር ድረስ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ በመቆየቱ ሠራተኞቹ ለዘርፈ ብዙ ቀውስ መዳረጋቸውን ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል ገልፀዋል።

የሥራ መብት በተለያዩ ዓለምአቀፍና አህጉርአቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች ዕውቅና ካገኙ መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች አንዱ መሆኑን የሚጠቅሰው ኢሰመኮ የሠራተኞች ደመወዛቸውን በሙሉና በወቅቱ የማግኘት መብትንም የሚጨምር እንደሆኑ አመልክቷል።

የዓለምአቀፉ የሥራ ድርጅት ደንቦችም ደመወዝ ሳይስተጓጎል ሊከፈል እንደሚገባና ክፍያቸው በወር ወይም በዓመት ተወስኖ የተቀጠሩ ሠራተኞች ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ ሊከፈሉ እንደሚገባ እንደሚደነግጉ ተገልጿል።

ይህ መብት በሀገራዊ ሕጎች ዕውቅና ያገኘ እና በፌዴራል የመንግሥት አዋጅም የተረጋገጠ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ብራይትማን ደመወዝ በወቅቱ አለመክፈል የሰብዓዊና የሥራ መብት ጥሰት እንደሆነ ተናግረዋል።

ምዕራብ ባድዋቾ ወረዳና ጎምቦራ ወረዳ ውስጥ ከዘጠኝ ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተቆራረጠ ክፍያ እና ካለፈው ነኀሴ አንስቶ ምርመራው እስከ ተከናወነበት እስካለፈው ወር ጊዜ ድረስ ደመወዝ ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ምክንያት ለከፋ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች መጋለጣቸውን መረዳቱን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል።

ሠራተኞቹ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የዕለት ጉርስ ለማግኘት መቸገራቸውን፣ የቤት ኪራይ መክፈል እንዳልቻሉ፣ የቤት ዕቃ ከመሸጥ ጀምሮ በተለያዩ የጉልበት ሥራዎች ላይ ተሠማርተው እንደሚገኙ፣ በአካባቢው ያሉ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ለመንግሥት ሠራተኞች ብድር መስጠት ማቋረጣቸውን የኢሰመኮ ሪፖርት ይናገራል።

በምሥራቅና በምዕራብ ባድዋቾ ወረዳዎች ከመቶ ሺህ በላይ ህፃናት ከትምህርት ውጭ መሆናቸውን፣ የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ አሥር የጤና ጣቢያዎችና 49 የጤና ኬላዎች ሥራ በመስተጓጉሉ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚሆን ሰው አገልግሎት እንደተቋረጠበት ተገልጿል።

አንድ የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኛ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ደመወዝ በመቋረጡ ሆስፒታሉ ባለፈው ጥቅምት ተዘግቶ እንደነበር ገልፀዋል።

ምርመራው ባካለላቸው አካባቢዎች የመምህራን ደመወዝ በመቋረጡ በሾኔ ከተማ አስተዳደር፥ በምሥራቅ ባድዋቾ፥ በምዕራብ ባድዋቾና በጎምቦራ ወረዳዎች ውስጥ የተመዘገቡ ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ተማሪዎች በምርመራው ወቅት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደነበሩ ኢሰማኮ አመልክቷል።

በደህንነት ሥጋት ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የሾኔ መምህር ለሦስት ተከታታይ ወራት እንዳልተከፈላቸው ተናግረዋል።

ቅሬታና አቤቱታ ያሰሙ ማስፈራራት፣ ዛቻ፣ ድብደባና እሥራትም ጭምር እንደደረሰባቸው የቀረቡ ስሞታዎችን የኢሰመኮው ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል አረጋግጠዋል።

የዞንና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለሥልጣናትን ምላሽና አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ይሁን እንጂ የተለያዩ የአካባቢው አመራር አባላት ለአሜሪካ ድምፅ ቀደም ሲል በስልክ ሰጥተውት በነበረ ቃል ችግሩ መኖሩን አምነው ከማዳበሪያ ዕዳ ጋራ በተያያዘ የተፈጠረ የበጀት እጥረት ያስከተለው መሆኑን ተናግረው ነበር።

የአካባቢው መንግሥት የተለሳለሰ ጥረት ማድረጉን የሚጠቅሰው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት ሁሉም ክልሎች ተገቢ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡