በምሥራቅ አፍሪካ ትላንት እሁድ በበርካታ ሃገራት የኢንተርኔት መቋረጥ ተከስቶ እንደነበር ታውቋል።
ኔት ብሎክስ የተሰኘውና በዓለም የኢንተርኔት ስርጭትን የሚከታተለው ድርጅት እንዳስታወቀው በባህር ሥር በተዘረጉ መሥመሮች ላይ በደረሰው ጉዳት፣ በተለይም በታንዛኒያ እና በፈረንሳይ ሥር በምትተዳደረው ማያት ደሴት ከባድ መቁራረጥ ተከስቶ እንደነበር ድርጅቱ አስታውቋል።
ችግሩ የተከሰተው ከሞዛምቢክ እስከ ደቡብ አፍሪካ በተዘረጋው መሥመር ላይ እንደሆነ የታንዛኒያ የመረጃ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሞዛምቢክ እና ማላዊ መካከለኛ የሚባል መቋረጥ ሲደርስባቸው፤ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ኮሞሮስ እና ማዳጋስካር አነስተኛ የሚባል መቋረጥ ደርሶባቸዋል ተብሏል።
በኬንያ አገልግሎቱ መልሶ ቢጀምርም፣ አገልግሎቱ የተቆራረጠ እንደሆነ ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።
የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ሴራ ሊዮንም ችግሩ ደርሶባት እንደነበር ታውቋል።