በተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢዎች ሰሞኑን እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ብዙ ሕይወት ማጥፋቱና በመቶዎች ሺሆች የሚቆጠር ሰው ማፈናቀሉ እየተነገረ ነው።
በከበደው ዶፍ በብዛት እየተጎዱ ያሉት ኬንያ፣ ሶማሊያና ርዋንዳ መሆናቸው ታውቋል።
የአሁኖቹ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋዎች እየደረሱ ያሉት አካባቢው ሚሊዮኖችን ለረሃብና ለበሽታ ዳርጎ ሲያስፈራ ከነበረው ካለፈው ዓመት የበረታ ድርቅ ለማገገም እየጣረ ባለበት ወቅት ነው።
ኬንያ፣ ርዋንዳና ሶማሊያ ውስጥ በጎርፍ ምክንያት የሞተው ሰው ቁጥር ከአራት መቶ በልጧል።
ርዋንዳ ውስጥ ብቻ ባለፉት አራት ወራት ቁጥሩ ከሁለት መቶ በላይ የሆነ ሰው መሞቱን የሃገሪቱ የአደጋ አያያዝ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከሞቱት መካከል አሥራ ስምንቱ ላይ ጉዳት የደረሰው በዚህ ወር ውስጥ በተፈጠሩ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ምክንያት ነው።
ሶማሊያ ውስጥ ጁባና ሸበሌ ወንዞች ገደፎቻቸውን እያለፉ የሚፈስሱባቸውን አካባቢዎች አጥለቅልቀዋል።
ሁኔታው ሰዉን ለበሽታና ለረሃብ ያጋለጠው መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የሶማሊያ ኃላፊ ጀስቲን ብሬዲ ገልፀዋል።
“ሳይክሎን ሳጋር” የሚል ስያሜ የተሰጠው የውቅያኖስ ማዕበል ባለፈው ሣምንት መጨረሻና በዚህ ሣምንት መጀመሪያ አካባቢ ሶማሊያን ሲመታ ቢያንስ 13 ሰው ሞቷል።
የአሁኑ ማዕበል የመታቸው የፑንትላንድ፣ የሶማሊላንድና የጅቡቲ አካባቢዎች ባለፉት ሦስት ዓመታትም እጅግ የበረታ ድርቅ የዋለባቸው እንደነበሩ ብሬዲ አስታውሰው በዚህም ምክንያት እንዲህ ዓይነቱን ጉዳት የመቋቋም አቅም እጅግ የተዳከመ መሆኑን ገልፀዋል።
የኬንያ ቀይ መስቀል ማኅበር ባወጣው ሪፖርት ደግሞ በዶፉ ምክንያት ቢያንስ የሁለት መቶ ሰው ሕይወት መጥፋቱን አመልክቷል።
ከከባዶቹ ጉዳቶች አንዱ የሆነው አርባ ስምንት የሞተበት አደጋ የደረሰው ናይሮቢ አቅራቢያ የሚገኝ ግድብ በመሰበሩ ምክንያት መሆኑ ተዘግቧል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5