አዲስ አሕጉራዊ የጋራ የበረራ አገልግሎት ሊጀመር ነው

በምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ አዲስ ለሚከፈቱ የበረራ መሥመሮችና ለሃገሮቹ ለሚሠጥ ተጨማሪ ድጋፍ የኢትዮጵያ፣ የደቡብ አፍሪካና የግብፅ አየር መንገዶች በጋራ ሆነው ለመሥራት እየተነጋገሩ ነው፡፡

የሦስቱ ሃገሮች አየር መንገዶች ለምዕራብ አፍሪካ የሚከፍቱት አገልግሎት በቅርብ ወራት ሥራ እንደሚጀምር የደቡብ አፍሪካው አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሲዛ ምዚሜላ ጆሃንስበርግ ለሚገኘው ሴክ24 ለሚባለው የዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዶቹ የሚጀምሩት አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ይቀርባል የተባለው በምሥራቅና በምዕራብ አፍሪካ ሃገሮቹ በጋቦን፣ በካሜሩን፣ በቻድ፣ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ፣ በሳዖ ቶሜና ፕሪንሲፔ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ነው፡፡

ስለዚህ ስምምነት ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ግርማ ዋቄ የታላቁ ዓለም አቀፍ የበረራ መረብ የስታር አላያንስ በአፍሪካ ብቸኞቹ አባል የሆኑት እነዚህ ኩባንያዎች የሚጀምሩት የበረራ አገልግሎት አለመሆኑን ገልፀው አሁን አየር መንገዶቹ የሚገኙት ሁኔታውን በማጥናት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የጥናቱ ውጤት ታይቶም ሁሉም ወገኖች ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕቅድ እንደሚዘጋጅ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ግርማ ዋቄ አመልክተዋል፡፡

አሁን ለጊዜው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይዞታ የሆነው "አፍሪካን ስካይ" ወይም "አስካይ" ቶጎ ውስጥ እየሠራ ስለሆነ የእርሱን አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል ገልፀው ጥናቱ አልቆ ሲስማሙበት አንድ ዓይነት ስትራተጂ ወደማሙጣት እንደሚሄዱ አስረድተዋል፡፡

ይህ ሦስቱ አየር መንገዶች የሚጀምሩት አገልግሎት የሚኖረው ድርሻ አነስተኛ ነው ስለመባሉ ስለሥራዎቹም አቶ ግርማ ሲናገሩ እነርሱ የሚያከናውኑት የአስተዳደርና የቴክኒክ ድጋፍ አሁን በተጠቀሱት ሃገሮች ውስጥ ላሉት አየር መንገዶች መስጠትና የበረራ አገልግሎት በሌለባቸው ቦታዎችም አዳዲስ መሥመሮችን በጋራ መዘርጋት እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ አቶ ግርማ ዋቄን ያነጋገራቸው ሰሎሞን አባተ ዝርዝሩን በዘገባው አስፍሯል፤ ያድምጡት፡፡