የሪፐብሊካን ፓርቲ ትላንት ማክሰኞ በተካሄደው ምርጫ ከ100 መቀመጫዎች ካሉት የዩናይትድ ስቴትስ የእንደራሴዎች ምክር ቤት (ሴኔት) ቢያንስ የሃምሳ አንዱን ማሸነፋቸው ይፋ ተደርጓል። አሁን ሪፕብሊካኖች የሚቆጣጠሩት የተወካዮች ምክር ቤት እጣ ግን አልለየም።
435 ጠቅላላ መቀመጫዎች ያሉት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመላዋ ዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ለሁለት ዓመታት ለሚዘልቅ የሥራ ዘመን ሲወዳደሩ፤ በየ6 ዓመቱ አባላቱ ለአዲስ ምርጫ የሚፎካከሩበት የእንደራሴዎች ምክር ቤት በበኩሉ፤ 34 መቀመጫዎች ብቻ ናቸው ለዘንድሮው ምርጫ የቀረቡት።
የትላንቱ ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ ዲሞክራቶች ሴኔቱን (የእንደራሴዎች ምክር ቤቱን) በጠባብ ብልጫ ሲቆጣጠሩ፤ ሪፐብሊካኖች ደግሞ በተመሳሳይ አነስተኛ ብልጫ (220 መቀመጫዎችን በመያዝ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን እንደቆጣጠሩ ናቸው።
በሌላ በኩል በዌስት ቨርጂኒያ እና ኦሃዮ ክፍለ ግዛቶች የሴኔት መቀመጫዎችን ያሸነፉበት ወሳኝ ድል የሪፐብሊካን ፓርቲያቸውን ዳግም አብላጫ መቀመጫዎች እንዲቆጣጠር አስችሎታል።
የካሊፎርኒያ ክፍለ ግዛት ምርጫ ድምጽ ቆጠራ ብዙ ቀናት የሚወስድ መሆኑ፤ አሸናፊው ያልለየባቸው ፉክክሮች ዳግም ምርጫ እና በጣም ተቀራራቢ ውጤቶች የተገኙባቸው ምርጫዎች ዳግም ቆጠራም ሳምንታት ሊወስዱ የመቻላቸው እጣ ተደማምሮ፤ የተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ውጤት ለበርካታ ቀናት ሳይታወቅ ሊቆይ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
የምርጫ ቅስቀሳዎች እየተካሄዱ ሳሉ የተደረጉ የፖለቲካ ግምገማዎች ለሁለቱ ምክር ቤቶች ተመራጮች ያለው ድጋፍ፤ ለፕሬዚደንትነት የተፎካከሩት ካማላ ሃሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሃውስ ለመዝለቅ ሲያደርጉት በነበረው ብርቱ ፉክክር የታየውን የመሰለ የፓርቲ መስመር የተከተለ ሆኖ ታይቷል።
በጥቅምት ወር የሮይተርስ የዜና ወኪል እና ኢፕሶስ በጋራ ያካሄዱት የሕዝብ አስተያየት ግምገማ እንዳመለከተው ከጠቅላላው የተመዘገቡ መራጮች 43 በመቶው በየምርጫ ክልሎቻቸው ያሉ ሪፐብሊካን የምክር ቤት አባላትን ሲደግፉ፣ በተመሳሳይ 43 በመቶው መራጮች የዲሞክራት ፓርቲውን እንደሚደግፉ አሳይቷል።