‘ባይደን ፕሬዝዳንታዊ ሥልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው’ - ትራምፕ

ፎቶ ፋይል፦ የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት እና የሪፐብሊካን ፕሬዝዳንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጥቅምት ወር መገባደጂያ ከሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸው በትላንትናው እለት ይፋ ባደረጉ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ፣ የቀድሞው ተቀናቃኛቸው የሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ ከፕሬዝዳንታዊ ሥልጣናቸውም እንዲለቁ ጠይቀዋቸዋል።

“እምነት የማይጣልባቸው ጆ ባይደን በፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ለመወዳደር ብቁ አልነበሩም፤ በእርግጠኝነትም በፕሬዝዳንትነት ለማገልገልም ፈጽሞ ብቁ አይደሉም” ሲሉ፤ ትራምፕ ለምርጫ ዘመቻቸው የሚውል አዲስ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ጥረት ያካተተ መግለጫ በማሕበራዊ ሚዲያ አሰራጭተዋል።

ባይደንን “በሀገራችን ታሪክ ከሁሉ የከፉት ፕሬዝዳንት” ሲሉ የጠሯቸው ትራምፕ “ፍፁም አሳፋሪ በሆነ መንገድ የምረጡኝ ዘመቻቸውን አቋርጠው ወጥተዋል” ብለዋል። የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ማይክ ጆንሰን እና ሌሎች ለትራምፕ ታማኝ የሆኑ ሪፐብሊካን የምክር ቤት ባላትም ይህንኑ ትራምፕ ያቀረቡትን ጥሪ አስተጋብተዋል።

“ጆ ባይደን ለምርጫ ውድድሩ ብቁ ካልሆኑ፣ በፕሬዝዳንትነት ለማገልገልም ብቁ አይሆኑም። እናም ሥልጣናቸውን በአስቸኳይ መልቀቅ አለባቸው። ምርጫው የሚካሄድበት ጥቅምት 26, 2017ዓም በሚፈለገው ፍጥነት አይደርስምና” ሲሉ ጆንሰን ባወጡት መግለጫ ዘርዝረዋል።

በምክር ቤቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ የሥልጣን እርከን በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኤሊሴ ስቴፋኒክም በበኩላቸው “ጆ ባይደን በዳግም ምርጫው ለመወዳደር ካልቻሉ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሆኖ ለማገልገልም ብቁ አይደሉም። በአስቸኳይ ሥልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው” ሲሉ ተመሳሳይ ጥሪ አስተጋብተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ “ባይደን ሥልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው የሚለው የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላቱ የሚያሰሙት ጥሪ ከሕግ አንጻር ምንም ዓይነት መሰረት የለውም” ያሉት በጤና፣ የጸጥታ ጉዳዮች እና ለሁሉም አሜሪካውያን እድል መፍጠር በሚያስችሉ ከሁለቱም ፓርቲዎች በተመረጡ ሃሳቦች ላይ በሚሰራው “ባይፓርቲዛን ፖሊሲ ሴንተር” በተባለው የጥናት ቡድን ‘የዲሞክራሲያዊ መዋቅሮች ጥናት’ ክፍል ድሬክተር ማይክል ቶሪንግ ናቸው።

ድሬክተሩ አያይዘውም “አንድ ፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ በሥራው ለመቀጠል፣ በዳግም ምርጫው እንዲሳተፍ የሚጠይቅ ምንም ዓይነት አስገዳጅ ሕገ መንግስታዊ ሁኔታ የለም” ብለዋል።

የአሜሪካ ድምጽ የሪፐብሊካኑን ጥያቄ አስመልክቶ አስተያየት ፍለጋ ላቀረበው ጥያቄ የዋይት ሃውስ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።