የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የጤና ድርጅት ሰባኛ ጠቅላላ ጉባዔ የኢትዮጵያውን ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን የድርጅቱ ስምንተኛ ዋና ዳይሬክተር እንዲሆኑ ዛሬ፤ ግንቦት 15/2009 ዓ.ም መርጧቸዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ የተመረጡት ከ194ቱ የዓለም የጤና ድርጅት አባል መንግሥታት መካከል ድምፅ የመስጠት መብት ካላቸው ከ185ቱ የ121ዱን ድምፅ አግኝተው ነው፡፡
ካናዳዊቱን የሆንግ ኮንግ ተወላጅ ማርጋሬት ቻንን የሚተኩት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ድርጅቱን በመምራት የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሆናቸው ነው፡፡
የዶ/ር ቴድሮስን ዕጩነት ሲደግፉና ሲቃወሙ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን በመላው ዓለም በአካልም በማኅበራዊ መገናኛዎችም ሰፊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ሰላማዊ ሰልፎች ተደርገዋል፡፡
ዘላለም ተሰማ የሚባሉ የለንደን ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊ የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ትናንት፤ ሰኞ ግንቦት 14 ሲከፈት ጄኔቫ ድረስ ሄደው የድርጅቱ አባል ሚኒስትሮች ፊት የተቃውሞ ድምፃቸውን በጩኸት አሰምተዋል፡፡
ዘርይሁን አበበ የሚባሉ የዶ/ር ቴድሮስ ዕጩነት ደጋፊና መመረጣቸውም ያስደሰታቸው ከአዲስ አበባ፤ እንዲሁም ቤልጅግ ብራስልስ የሚገኙት ተቃዋሚ ያሬድ ኃይለማርያም የየበኩላቸውን አስተያየቶች ለአሜሪካ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5