የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በአሜሪካ ድምፅ ቀርበው ለጥያቄዎቻችሁ በሰጡት መልስ የጋዜጠኝነት ሥራ ሙያውን መሠረት አድርጎ ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ ተሰጥቶ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ የምርመራ ጋዜጠኝነትና ልማታዊ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ በትክክል እንዲተገበር የበኩላቸውን ድርሻ ሲወጡ መቆየታቸውን ጠቁመው አሁን ወደ አዲሱ ሹመት ስለመጡ ያንን አሠራራቸውን እንደማይቀይሩ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ “ተቀይሯል” የሚል ሃሣብ ያላቸው አድማጭ “ዶ/ር ነገሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነትዎ ወጥተው የመንግሥት ሥልጣን ከተረከቡ አጭር ጊዜ ቢሆንም ሁሌም የሚሰጡትን መልስ ሳዳምጥ እስከአሁን በሥልጣንዎ የመንግሥታችንን ውሸትና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አድራጎቶች ያስተባብላሉ፡፡ ጋዜጠኞች፣ የፓርቲ መሪዎች፣ ደጋፊዎቻቸውና ሰላማዊ ሰዎች እሥር ቤት ውስጥ ናቸው፡፡ እርስዎ አሁን በአጠቃላይ ስላለው ሁኔታ ምን አስተያየት ይሰጣሉ? በኦሮምያና በአማራ ክልሎች በመንግሥቱ ኢ-ሰብዓዊ ሥራ ሕዝብ እየተንገላታ ነው፡፡ እውነቱ እናቶች ከነልጆቻቸው የታሠሩበት፣ ሴቶች ባሎቻቸውን፣ አባትና እናት ልጆቻቸውን፣ ሕዝብ እህት ወንድሙን የቀበረበት ሁኔታ ነው ያለው፤ ይህንን ለሕዝብ ማስተባበል ምን ይባላል? ባለሥልጣናቱ ሕዝብ አያውቅም ብለው ይገምታሉ ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የመንግሥቱ ቃል አቀባይ ዶ/ር ነገሪ ሲመልሱ “የመንግሥት ባለሥልጣናት ‘ውሸት፣’ እንዲሁም ‘ኢ-ዴሞክራሲያዊ አሠራር’ ለተባለው እኔ እንደማምንበት መንግሥትን ጠቅልሎ 'ውሸታም ነው' ማለት ትክክል አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በመንግሥቱ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ችግር ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ የማንቀበለውና ማንም ሥልጣኑን ተገን አድርጎ ሕዝብን እንዲጎዳ አናበረታታም፤ ሕጋዊም አይደለም፤ በሕገ-መንግሥቱም ሥር የወጡት ሕጎች ያንን አይደግፉም፤ አንዳንድ ግለሰቦች ሥልጠንን ተገን አድርገው ጉዳት ሲያደርሱ እንደነበረና ይህ ደግሞ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ እንዳስገደደው አሁን በጥልቀት መታደሱም ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሲገለፅ ቆይቷል” ብለዋል፡፡
እርሣቸው እዚያ ቦታ ላይ ያሉት “አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው” ያሏቸው ግለሰቦች የሚያደርጉትን ለማበረታታት ሳይሆን ከሌሎችም የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመሆን ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግሥትን በአጠቃላይ መኮነን አስቸጋሪ እንደሚመስላቸው ያመለከቱት ዶ/ር ነገሪ “ችግሮችን ነጥሎ በማውጣት ለዜጎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በየጊዜው ከሕዝቡ ጋር መሥራት ያስፈልጋል” ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል፡፡
ለዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ስፋት ያላቸው ጉዳዮችን የዳሰሱ ጥያቄዎች ናቸው የተነሱላቸው፡፡ ሙሉውን ቃለ-ምልልስ በአራት ክፍሎች ከተቀመጡት የድምፅ ፋይሎች ያዳምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
Your browser doesn’t support HTML5
Your browser doesn’t support HTML5
Your browser doesn’t support HTML5