የአሜሪካ ድምፅ በስልክ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ በ1977 ዓ.ም በተከሰተው ድርቅ ምክኒያት ከወሎ ተፈናቅለው ኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ከሰፈሩ ከ33 ዓመታት በኋላ ከኖሩበት አካባቢ በኃይል ተፈናቅለው ለችግር መዳርጋቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።
በስልክ ያነጋግረናቸውና በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል በቆቦ ከተማ እንደሚገኙ የገለፁልን የተለያዩ ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ከ33 ዓመታት በፊት የ1977 ዓ.ም በደርግ የሥልጣን ዘመን ከተከሰተው አስከፊ ረሃብ ለማምለጥ መንግሥት በወቅቱ ወለጋ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ አሁን በቄለም ወለጋ ዞን ፣ደንቢ ዶሎ ከተማ፣ ጫንቃ ፣ዓለም ተፈሪ፣ መቻራ ፣ጨቆርሳ፣ ሃዋ ገላን በተባሉ ከተማና ወረዳዎች እንዲሰፍሩ መደረጋቸውን ነው።
በዚህ ጊዜ ውስጥም ከአካባቢው የኦሮሞ ማኅበረሰብ ጋራ ደስታና ሐዘን ተጋርተው፣ንብረት አፍርተውና ኑሮን መስርተው ሲኖሩ እንደነበረ ይናገራሉ። ነገር ግን በጥቅምት 16 በድንገት በተፈጠረ ግጭት የአንዳንዶቹ ቤታቸው ተቃጥሎ የአንዳንዶቹ ደግሞ ቃጠሎው ወደ እነሱ እንዳይደርስ በፍርሃት አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውንና በአሁኑ ሰዓትም አማራ ክልል ውስጥ መጠለያ አተው በችግር ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ጽዮን ግርማ ተፈናቃዮቹን፣ በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው እየኖሩ ስጋት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩና፣ የአካባቢው ነዋሪዎችን አነጋግራ፣ የቆቦ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤትን ኃላፊን ጠይቃ ያዘጋጀችውን ዘገባ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5