አሮጌው 2012 አልቆ አዲሱን 2013 ልንቀበል የሰዓታት እድሜ ቀርቶናል። ለወትሮው ይህ አዲስ አመት ሲመጣ የሀገሪቱ እምብርት ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ትሞላለች፣ ትደምቃለች፣ በዓል በዓል ትሸታለች። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና ከሰሞኑ የታዩ አለመረጋጋቶች ጥላውን ያጠላበት የዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል ግን ከወትሮው የቀዘቀዘ መሆኑን የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ይገልፃሉ። ለበዓሉ መዳረሻ ድምቀት ይሰጡ የነበሩ የሙዚቃ ድግሶች፣ የንግድ ትርኢቶችና የተለያዩ ባዛሮች አለመኖራቸው የእንቁጣጣሽ በዓሉን ከማደብዘዝ ባሻገር በዝግጅቱ ይሳተፉ የነበሩ ተቋማት ጥቅም እንዳጡም ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ነዋሪዎችንና የንግድ ተቋማትን አነጋረን የዘንድሮ ዘመን መለወጫ አጠቃላይ ስሜትና የነዋሪዎችን ተስፋ የሚዳስስ ዘገባ ይዘናል።
ለወትሮው እንቁጣጣሽን ወይም አዲሱን የዘመን መለወጫ በዓል ለመቀበል አዲስ አበባ ግርግሯን የምትጀምረው ቀደም ባላ ነው። በከተማዋ በየመንገዱ ላይ የሚታዩ ግርግሮች፣ የሙዚቃ ትዕይንቶች፣ የግብይት ስርዓቶች፣ የንግድ ትርኢቶችና ባዛሮች ለበዓሉ መዳረሻ ትልቅ ድምቀት ይሰጡት ነበር። በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተያዘው ሰው ቁጥር 60 ሺህ ባለፈበት ወቅት የሚከበረው የዘመን መለወጫ ግን እነደተለመደው በደማቅ አቀባበል የታጀበ አለመሆኑን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልፀውልናል።
ከነዚህ አንዷ በአዲስ አበባ ልደታ አካባቢ ነዋሪ የሆነችው መሰረት ሰኢድ ናት።መሰረት የዘንድሮው ዘመን መለወጫ ስሜቱ በጣም የቀዘቀዘ ነው ትላለች።
የዘመን መለወጫ ድባብ ይቀንስ እንጂ የበዓሉን መቃረብ ተከትሎ የአዲስ ዓመት ብሥራትን የሚያውጁ ባህላዊ ሙዚቃዎች ግን አሁንም በየቦታው ይሰማሉ፣ አንዳንድ ህንፃዎች በአደይ አበባና በቢጫ ቀለማት ተውበው ይታያሉ። በገበያ ቦታዎችም ወረርሽኙን ለመግታት የተጣለውን የአካል መራራቅ የጣሱና ጥንቃቄ የጎደላቸው ግብይቶች ይካሄዳሉ ያለችን ደግሞ በጀሞ አንድ ነዋሪ የሆነችው መዓዛ ግርማ ናት።
ለመዓዛና ቤተሰቧ የዘንድሮውን በዓል እጅጉን ያቀዘቀዘው እንደተለመደው ከቤተሰብ ጋር አለመሰባስሰባቸው መሆኑን መዓዛ በቅሬታ ብትገልፅም፣ አዲሱን አመት ግን በተስፋ እንደምትቀበለው ትገልፃለች።
የዘመን መለወጫና ሌሎች በዓላትን ትልቅ ድምቀት በመስጠት በዓሉን በዓል ከሚያስመስሉ ዝግጅቶች ቀዳሚውን ቦታ የሚይዙት የንግድ ትዕይንቶች፣ የባዛር ዝግጅቶችና የሙዚቃ ኮንሰርቶች ናቸው። በዘንድሮ በዓል ግን ሁሉም አለመኖራቸው የበዓሉን ድባብ ለውጦታል ያሉን ከአዲስ አበባ የኢግዚብሽን ማዕከል ጋር በመተባበር ከ20 አመት በላይ የባዛር ትዕይንቶችን የሚያዘጋጀው የሴንቸሪ ፕሮሞሽን ሰርቪስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘውገ ጀማነህ ናቸው።
በአዲስ አበባ ኢግዚቢሽን ማዕከል በዓላትን አስታከው የሚደረጉ የባዛር ዝግጅቶችና የሙዚቃ ትዕይንቶች በኮሮና ምክንያት ሲሰረዙ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው። ከ 400 በላይ የንግድ ድርጅቶችንና በቀን ከ 20 ሺ በላይ ጎብኚዎችን የሚያሳትፈው ዝግጅት በሳለፍነው የፋሲካ በዓል በመሰረዙ ምክንያት ሴንቸሪ ፕሮሞሽን እሰከ 4 ሚሊዮን የሚጠጋ እንደገጠመው አቶ ዘውገ ያስረዳሉ።
ከንግድ ትርኢትና ባዛር በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ የሙዚቃና የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶችን የሚያዘጋጁ ተቋማትንም ክፉኛ ጎድቷል። ኮንሰርቶችና የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ይሳቃል ኢንትርቴይንመንት መስራችና ባለቤት እዮብ አለማየሁ ይሄ በታሪክ የሚነገር ሌላ ዘመን ነው ይላሉ። ይሳቃል ኢንተርቴይመንት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ድርጅቱ ለአንድ አመት ያቀዳቸውን ዝግጅቶች ማካሄድ ባለመቻሉ ትልቅ ኪሳራ እንደደረሰበት አቶ እዮብ ይገልፃሉ።
የዘንድሮው በዓል ድባብ ከወትሮው ይቀዝቅዝ እንጂ ነዋሪዎች አዲሱን አመት የሚቀበሉት በጉጉት ነው። አዲሱ ዘመን የኮሮና በሽታ የሚጠፋበት ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ በአጠቃላይ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት የሚመጣበት፣ ህዝቡ አንድነትን የሚያጎልብትበት የተሻለ አመት እንዲሆንም ተመኝተዋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5