የመንገዶች መዘጋት ለተለያዩ ችግሮች እንዳጋለጣቸው የደራ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ

Your browser doesn’t support HTML5

የመንገዶች መዘጋት ለተለያዩ ችግሮች እንዳጋለጣቸው የደራ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ

በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘውን ደራ ወረዳ ከአጎራባች አካባቢዎች የሚያገናኙ መንገዶች ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ በታጠቁ ኃይሎች ተዘግተው መቀጠላቸውን የገለጹ ነዋሪዎች፣ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል በምትገኘው ፍቼ ወረዳና በአማራ ክልል በሚገኘው መራቤቴ ወረዳ በኩል ወደ አገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ የሚወስዱ መንገዶች፣ “ተጓዦችን ለዝርፊያ፣ለእገታና ለሞት የሚዳርጉ ናቸው” በማለትም ነዋሪዎቹ አማረዋል።

ከአንድ ወር በፊት በመራቤቴ ወረዳ በኩል ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበሩ ስምንት የንግድ መኪና አሽከርካሪዎች በፋኖ ታጣቂዎች ከታገቱና የተጠየቁትን የማስለቀቂያ ቤዛ ከከፈሉ በኋላ መገደላቸውን፣ ኹኔታውን በቅርብ እንደሚያውቁ የተናገሩ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

“በመራቤቴ በኩል ለመጓዝ የሚሞክሩ አሽከርካሪዎች ገንዘብ እየከፈሉ እንደሚያልፉ አውቃለሁ” ያሉት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ከፍያለው አደሬ፣ተገደሉ ስለተባሉት ስምንት አሽከርካሪዎች ግን መረጃው እንደሌላቸው ጠቅሰዋል።

ዋና አስተዳዳሪው ዛሬ ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ ባደረጉት የስልክ ቃለ ምልልስ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በዞኑ አምሰት ወረዳዎች ፣ የፋኖ ታጣቂዎች ደግሞ በሦስት ወረዳዎች ውሰጥ እንደሚንቀሳቀሱ ጠቅሰው ለመንገዶቹ መዘጋትና በአካባቢው ላለው የጸጥታ ችግርም ሁለቱን ቡድኖች ተጠያቂ አድርገዋል።

የአሜሪካ ድምፅ በስምንት አሽከርካሪዎች ላይ ተፈፀመ የተባለውን እገታና ግድያ እንደዚሁም ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆነውን አካል ማንነት ከገለልተኛ ወገን አላረጋገጠም።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትና የፋኖ ታጣቂ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለተመሳሳይ ውንጀላዎች በሰጧቸው ምላሾች፣ ታጣቂዎቻቸው ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ እንደማያደርጉ በመግለፅ በጽኑ አስተባብለዋል።