መጠለያ የቸገራቸው የመጠለያ ጣቢያ ተፈናቃዮች

Your browser doesn’t support HTML5

መጠለያ የቸገራቸው የመጠለያ ጣቢያ ተፈናቃዮች

ለረጅም ጊዜ በዘለቀውና ከፍተኛ መጠን ባለው የበልግ ዝናም ምክንያት ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን፣ በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ገለጹ፡፡

ተፈናቃዮቹ፥ ከመጠለያው ባሻገር ይሰጣቸው የነበረው የምግብ ድጋፍ ከተቋረጠ ሁለት ወር እንዳለፈው ይናገራሉ፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት፣ ከተማዋ ከዐቅሟ በላይ ተፈናቃይ መያዟ፣ በራሱ በተፈናቃዩ እና በከተማዋ ላይ ተጽእኖ እንዳስከተለ ጠቅሰው፣ የበጎ አድራጊ አካላትን ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡

SEE ALSO: የቤተሰብ ሓላፊነት የወደቀባት ወጣት ተፈናቃይ

በዐማራ ክልል የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዲሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ በበኩላቸው፣ በክልሉ ከ660 ሺሕ በላይ ተፈናቃይ መኖሩን ጠቁመው፣ ሰብአዊ ድጋፍ አድራጊዎች፣ ለሰሜኑ ጦርነት ተጎጂዎች የለገሱትን ያህል ሰብአዊ ድጋፍ ለተፈናቃዮቹ እያደረጉ እንዳልኾነ ገልጸዋል፡፡

አዛውንቷ መዲና ታደሰ፣ ዕድሜያቸውን በትክክል ባያውቁትም 70 ዓመት ይኾነኛል፤ ይላሉ። ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ አኖ አካባቢ ተፈናቅለው፣ ደብረ ብርሃን በሚገኘው ቻይና መጠለያ ካምፕ ውስጥ መኖር ከጀመሩ ሁለት ወር ኾኗቸዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ ዞኖች እና ወረዳዎች የመጡት ተፈናቃዮች፣ እነርሱ ኦነግ ሸኔ ሲሉ የሚጠሩትን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ፥ ለግድያው፣ ለአካል ጉዳቱ፣ ለንብረት ዘረፋው እና ለመፈናቀሉ ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

SEE ALSO: ደብረ ብርሃን የሰፈሩ ተፈናቃዮች እያማረሩ ነው

መኖሪያቸውን በቨርጂኒያ ያደረጉት የታጣቂዎቹ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አፋን ኦሮሞ ዝግጅት ክፍል በተደጋጋሚ በሰጡት ቃል፣ ታጣቂዎቻቸው በመንግሥት ወታደሮች ላይ እንጂ በሰላማውያን ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙ ገልጸው በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።

ተፈናቅለው ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያደርግላቸው የምግብ ድጋፍ ከረኀብ ቢታደጋቸውም፣ ተጨናንቀን እንኖርበታለን ያሉት ድንኳን፣ ከሚጥለው ዝናም አልተከላከለልንም፤ ብለዋል፡፡

ከወለጋ አኖ አካባቢ የመጡት ሌላዋ የዕድሜ ባለጸጋ ፋጢማ አሰን ናቸው፡፡

የአራት ልጆች እናት እና የአራት ልጆች አያት መኾናቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ፋጢማ፣ በአካባቢያቸው በደረሰው የጸጥታ መደፍረስ ሳቢያ፣ ከልጆች እና ከባለቤታቸው ተነጥለው አንድ ልጃቸውን ይዘው ወደ ደብረ ብርሃን ከመጡ ወር እንዳለፋቸው ገልጸዋል፡፡

በሚጥለው ዝናም ለችግር መዳረጋቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ፋጢማ፣ የምግብ ርዳታ በበቂ አለመቅረቡ ችግራቸውን እንዳባባሰው ገልጸዋል፡፡

ከምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ የመጡት ጌትዬ ደርቤ፣ ተፈናቃዩ የምግብ ድጋፍ ከአገኘ ሁለት ወር እንዳለፈው አስታውቀዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ፣ እየጣለ ካለው ዝናም እና ከመጠለያው አለመመቸት ጋራ ተያይዞ፣ ለተላላፊ በሽታ እንጋለጣለን፤ የሚል ስጋትም አላቸው፡፡

ከተማዋ ከዐቅሟ በላይ ተፈናቃዮችን አስተናግዳለች፤ የሚሉት የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት፣ ይህም ተፈናቃዩንና አካባቢውን ለውስብስብ ችግር ዳርጓል፤ ብለዋል፡፡

SEE ALSO: ደብረ ብርሃን የሚገቡ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ ነው

የከተማ አስተዳደሩ፣ ባቄሎ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ፣ ለተፈናቃዮች መጠለያ ግንባታ መጀመሩን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ከወራት በፊት መግለጹ ተዘግቧል፡፡

መጠለያው ግን፣ በከተማዋ ውስጥ ያሉትን 30 ሺሕ ተፈናቃዮች መያዝ እንደማይችል ጠቁሞ፣ መንግሥት እና በጎ አድራጊዎች የመፍትሔው አካል እንዲኾኑ ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል። ምክትል ከንቲባ በድሉ፡-

በዐማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዲሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ፣ በተለይ ለጋሽ አካላት፣ በሰሜኑ ጦርነት ሰሞን የነበራቸውን ያህል እንቅስቃሴ አለማድረጋቸው፣ በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ ለከፋ ሰብአዊ ጉዳት መዳረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

በተወሰኑ አካላት ጥረት፣ በዐማራ ክልል በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች፣ በቂ መጠለያ እና ምግብ ለማቅረብ አዳጋች እንደኾነ ዲሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ከ660ሺሕ የሚልቁ ተፈናቃዮች፣ በ40 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ከእነዚኽም የሚበዙት፣ ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡