በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ፕሬዝደንታዊ ክርክር ተከናወነ

ምክትል ፕሬዝደንት ካመላ ሄሪስና በቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ መካከል የታቀደው የምርጫ ክርክር ማክሰኞ ምሽት በፊለደልፊያ ብሔራዊ የሕገ መንግስት ማዕከል ተካሂዷል።

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው፣ በምክትል ፕሬዝደንት ካመላ ሄሪስና በቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ መካከል የታቀደው የምርጫ ክርክር ማክሰኞ ምሽት በፊለደልፊያ ብሔራዊ የሕገ መንግስት ማዕከል ተካሂዷል።

ወደ ዶናልድ ትረምፕ ቀርበው እጅ የተጨባበጡት ካመላ ሄሪስ፣ በትረምፕ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ትችት ሰንዝረዋል። “በአሜሪካ ታሪክ ትልቅ የኢኮኖሚ ድቀት ተብሎ ከሚጠራው ‘ግሬት ዲፕረሽን’ ወዲህ ትልቁ ሥራ አጥነት የነበረበት ዘመን” ሲሉ ካመላ ሄሪስ የትረምፕን የአስተዳደር ዘመንን ነቅፈዋል።

“የአሜሪካ ሕዝብ፣ ከሚለያየን ይልቅ አንድ የሚያደርገንና ወደ አንድ የሚያመጣን ፕሬዝደንት እነደሚፈልግ አምናለሁ” ብለዋል ካመላ ሄሪስ።

“ለሁሉም አሜሪካውያን ፕሬዝደንት እንደምሆን ቃል እገባለሁ” ሲሉም አክለዋል ካመላ ሄሪስ።

ትረምፕ በበኩላቸው ፕሬዝደንት በነበሩበት ወቅት የሠሩትን ሥራ በማስታወስ ተከላክለዋል።

“የዋጋ ግሽበት በእኔ ጊዜ አልነበረም። በእነርሱ ጊዜ ግን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ነበር። ይህም ምናልባት በታሪካችን ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት ነው። ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት መጥፎ ጊዜ አላየሁም” ብለዋል ትረምፕ፡፡

“ሰዎች ወደ ገበያ ሄደው ሥጋም ሆነ እንቁላል ወይም ሌላ ነገር መግዛት አልቻሉም” ሲሉ አክለዋል ትረምፕ።

ሁለቱ እጩዎች በፍልሰተኞች ጉዳይም ተከራክረዋል። ካመላ ሄሪስ፣ ትረምፕ በሁለቱ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ የተደረሰበትን የፍልሰተኞች ሕግ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ሆነዋል ሲሉ ከሰዋል።

ትረምፕ በበኩላቸው፣ ካመላ ሄሪስ ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑበት የአሁኑ አስተዳደር ሕገ ወጥ ፍልሰትን ያበረታታል ሲሉ ከሰዋል።

“በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገቡ በማድረግ የማኅበረሰባችንን ድር እየበጣጠሱ ነው” ብለዋል ትረምፕ፡፡

“ወንጀል በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። አዲስ ዓይነት ወንጀል መጥቷል፣ ይህም የፍልሰተኞች ወንጀል ነው” ሲሉ ተናግረዋል ትረምፕ፡፡

የውጪ ጉዳይና የጋዛው ጦርነትም በክርክሩ ወቅት ተነስቷል።

“ይህ ጦርነት መቆም አለበት፡” ያሉት ሄሪስ፣ “የተኩስ ማቆም ስምምነት አስፈላጊ ነው። ታጋቾችም መለቀቅ አለባቸው” ብለዋል።

ካመላ ሄሪስ፣ ትረምፕ “በብሔራዊ ደህንነትና በውጪ ፖሊሲ ጉዳይ ደካማ ናቸው” ብለዋል።

ትረምፕ በበኩላቸው እርሳቸው ፕሬዝደንት ቢሆኑ ኖሮ በዩክሬን ያለው ጦርነት እንደማይጀምር ተናግረዋል። “ሩሲያ ወደ ዩክሬን አትዘልቅም ነበር” ሲሉም አክለዋል።

ሁለቱ እጩዎች ሲገናኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ ትረምፕ በ 2016 ከሂላሪ ክሊንተን ጋራ ካደረጉት ክርክር ወዲህ፣ ከሴት እጩ ጋራ ሲከራከሩ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

በአሜሪካ ብዙሃን መገናኛዎች ዳሰሳ መሠረት ሁለቱ እጩዎች ተቀራራቢ ድጋፍ አላቸው።