በቱርክ እና ሦሪያ የድንበር አካባቢ ትናንት ሰኞ በደረሰው ርዕደ መሬት ቢያንስ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ተገለጠ። ከሁለት ሳምንታት በፊት በዚያው የሁለቱ ሀገሮች ድንበር አካባቢ በመታው ኃይለኛ የመሬት ነውጥ ቁጥራቸው ወደ 45 ሺህ የሚጠጋ ሰዎች መግደሉ ይታወሳል።
የትናንቱ የመሬት መናወጥ በርዕደት መለኪያው በሪክተር ስኬል ላይ 6 ነጥብ 4 ያስመዘገበ ሲሆን የደረሰውም ከሁለት ሳምንት በፊት የደረሰው ርዕደት እጅግ ከባድ ጉዳት ባደረሰበት የሃታይ ክፍለ ግዛት ከተማ መሆኑ ተዘግቧል።
የትናንትናው ነውጥ ሦሪያ፣ ዮርዳኖስ፥ሊባኖስ፥ ግብጽን ጨምሮ በርካታ ሀገሮች ውስጥ የተሰማ ሲሆን ከመጀመሪያው በኋላ ሌላ በመለኪያው ላይ 6 ነጥብ 4 ኃይል ያስመዘገበ የመሬት ነውጥ መከተሉ ታውቋል።
ሃታይ ክፍለ ሀገር ውስጥ በርካታ ህንጻዎች የተደረመሱ ሲሆን የዕርዳታ ሰራተኞች ከፍርስራሹ ውስጥ መውጫ ያጡ በርካታ ሰዎችን እየፈለጉ ናቸው።
የሦሪያ ባለሥልጣናት በበኩላቸው አሌፖ ውስጥ ስድስት መጎዳታቸውን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬቺፕ ታይፕ ኤርዶዋን ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ጋር ተነጋግረዋል።
ከዚያ ቀደም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ብሊንከን ዩናይትድ ስቴትስ ለቱርክ እና ለሦሪያ የ100 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ዕርዳታ እንደምትሰጥ ቃል ገብተዋል። ይህም ለሁለቱ ሀገሮች የለገሰችውን ዕርዳታ ወደ 185 ሚሊዮን ዶላር ከፍ አድርጎታል።