ሴቶች እና ህጻናትን እንዲሁም ሁለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን ድንበር ላይ በተፈጸመ ጥቃት ተገደሉ። ከሁለቱ አገራት የድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዘ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2021 አንስቶ ከተቀቀሱ ግጭቶች ያሁኑ በገዳይነቱ የከፋው መሆኑን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ከደቡብ ሱዳኗ የዋራፕ ግዛት የተነሱ የታጠቁ ወጣቶች ባለፈው ቅዳሜ ጥር 18 ዓ.ም ወደ የአጎራባቿ አብዬ ግዛት አቅንተው ወረራ መፈጸማቸውን የማስታወቂያ ሚንስትሩ ቡሊስ ኮች ትላንት ሰኞ አስታውቀዋል። ከስልሳ በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የተናገሩት ኮች አክለውም በጥቃቱ ሳቢያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሀን ዜጎች በመንግስታቱ ድርጅት የጦር ካምፕ መሸሸጊያ ፍለጋ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል አባል የሆኑ አንድ ጋናዊ እና አንድ የፓኪስታን ዜጋ በተከታታይ ቀናት በተፈጸሙ ጥቃቶች መገደላቸውን በመንግስታቱ ድርጅት የአብዬ ጊዜያዊ የፀጥታ ኃይል አስታውቋል።
የዋራፕ ግዛት የማስታወቂያ ሚንስትር በበኩላቸው መንግስታቸው ከአበዬ አስተዳደር ጋር በመሆን በጋራ ምርመራ እንደሚያካሂድ ተናግረዋል።
በአብዬ ከድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጦች ከፍተኛ መጠን ያለው ቀረጥ ከሚሰበሰብበት አስተዳደራዊ ወሰን ጋር ተያይዞ በሚነሳ ውዝግብ ሳቢያ በዲንቃ ብሔረሰብ ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች ይቀሰቀሳሉ። በነዳጅ ሃብቷ የምትታወቀው አብዬ የይገባኛል ይዞታ በሚያነሱት ሁሉቱ አገሮች በጋራ የምትተዳደር ግዛት መሆኗም ይታወቃል።
በሌላ በኩል፡ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ነፃነቷን ካገኘች በኋላ የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች መገደል እና ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክኒያት መሆኑም አይዘነጋም።