(ይህ ገፅ ሲከፈት የተደራረቡ ወይም የተረበሹ ድምፆችን የሚሰሙ ከሆነ ኮምፕዩተርዎ ከአንድ በላይ ድምፅ ማጫወቻ አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ፅሁፍ ሥር ካሉት ማጫወቻዎች አንደኛውን ብቻ አስቀርተው ሌሎቹን ያቁሟቸው፡፡)
በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢዋ እንዲሁም በሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ እና የመፍትሔ አፈላላጊው ኮሚቴ አባላትና ሌሎችም የታሠሩ ሰዎች እንዲፈቱ በመጠየቅ ዛሬ ሰልፍ አድርገዋል፡፡
ብዙ ወንዶችና ሴቶች የተገኙበት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ደጃፍ ላይ የተካሄደው ይህ ሠልፍ የተዘጋጀው አሜሪካ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ድርጅቶች መሆኑን ከአስተባባሪዎቹ አንዱ ገልፀዋል፡፡
ድርጅቶቹም በድር ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ፌዴሬሽን፣ ዋሽንግተን ዲ.ሲ. የሚገኘው ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን፣ ነጃሲ የፍትሕ ምክር ቤት (ነጃሺ ጀስትስ ካውንስል) ሰላም የኢትዮጵያዊያን ማኅበር ናቸው፡፡
በሠልፉ ላይ ከተገኙት መካከል የዋሽንግተን ዲ.ሲ.ው ፈርስት ሂጅራ ኢማም ሼህ ኻሊድ ዑመር ጥያቄዎቻቸው ለሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው ለኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል ያቀረባቸው ሦስቱ ጥያቄዎች መሆናቸውንና የአሜሪካ መንግሥት ጫና እንዲያደርግ እንደሚፈልጉ ገልፀዋል፡፡
በሠልፉ ላይ ክርስቲያኖችም አብረው የወጡ ሲሆን “የሙስሊሞቹ ጥያቄዎች ትክክል በመሆናቸው ድጋፋችንን ልንሰጣቸው፣ መታሠርና መደብደብም ስለገጠማቸው ያንን ለማውገዝ ወጥተናል” ብለዋል አባ ፊሊጶስ፣ የፔንሲልቬንያና የሜሪላንድ ሊቀ ጳጳስና በስደት ያለው ሲኖዶስም አባል፡፡
ሁለቱም የሃይማኖት አባቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ክርስትናና እሥልምና አብረው የኖሩ ሐይማኖቶች ሕዝቧም እንዲሁ በአንድነት የኖረ መሆኑን በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በሚሰጧቸው መግለጫዎች አሁን በቁጥጥር ሥር የሚገኙት ለሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና ጥቂት የሚሏቸው ሌሎች ሙስሊሞች የአክራሪነትን መንገድ የመረጡ ናቸው ይሏቸዋል፡፡
የመንግሥትን ወገን በመደገፍም ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጡ ሙስሊሞችም እንዲሁ አክራሪዎች ናቸው እያሉ መፈክር ያሰማሉ፤ ለመገናኛ ብዙኃንም ይናገራሉ፤ መንግሥት ይቅጣልን ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ይህንኑ ሁኔታ በቅርብ እየተከታተለው መሆኑን ገልፆ ሁሉም ወገኖች ጉዳዩን በትዕግሥት እንዲይዙት፤ ሕግን፣ የእምነት መብትና ነፃነትን እንዲያከብሩ ጠይቋል፡፡
ዝርዝሩን ከዘገባው ያዳምጡ፡፡
(ገፁ ሲከፈት የተደራረቡ ወይም የተረበሹ ድምፆችን የሚሰሙ ከሆነ ከዚህ ሥር ካሉት ማጫወቻዎች አንደኛውን ብቻ አስቀርተው ሌሎቹን ያቁሟቸውና የሚጫወተውን እንደገና ያስጀምሩት፡፡ )