“በሰላምም ይሁን በአመፅ - ነፃነት በአስፈላጊው መንገድ ሁሉ!” ይል ነበር ማልኮም ኤክስ በየንግግሩ አዝማች፤ እንደልማድም ሆኖበት፤ ደግሞም የነፃነትን አስፈላጊነት ለማፅናት፡፡
ጥቁሩ የመብቶች ተሟጋችና ታጋይ ማልኮም ኤክስ ልክ የዛሬ 52 ዓመት፤ (በኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር) የካቲት 14/1957 ዓ.ም ኒው ዮርክ ከተማ ላይ ንግግር እያደረገ ሳለ በተተኮሰበት ጥይት በሰላሣ ዘጠኝ ዓመት ዕድሜው መገባደጃ አካባቢ ተገደለ፡፡
በሃያ አንድ ዓመት ዕድሜው በዘረፋ ወንጀል ተከስሶ ወኅኒ በገባ ጊዜ ወጣቱ ማልኮም ኤክስ “ኔሽን ኦቭ ኢስላም” ወይም “እሥላማዊ መንግሥት” ይባል የነበረው ንቅናቄ መሪ የኤላይጃ ሙሐማድ የነደደ ተከታይ ሆነ፡፡ በኋላም የተዋጣለት የንቅናቄው መሪና ሰባኪ፤ ስሜት አቀጣጣይ ተናጋሪም ወጣው፡፡
የማልኮም ኤክስ የትግል ሥልት በዘመኑ በአሜሪካ ጥቁሮች ንቅናቄ ውስጥ እጅግ ተናኝቶ ከነበረውና ከሕንዳዊው ማኅትማ ጋንዲ ከተቀዳው የማርቲን ሉተር ኪንግ ሰላማዊ መሥመር በፍፁም የተለየ ነበር፡፡ ማልኮም ኤክስ እራስን መከላከልንና ከነጮች እራስን ማራቅን አበርትቶ ይመክር ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በኅዳር 1956 ዓ.ም በነፍስ ገዳይ ጥይት የወደቁ ጊዜ ማልኮም ኤክስ ሁኔታውን ጣል ጣል አድርጎ ሲናገር የ“ኔሽን ኦቭ ኢስላም” መሪው ኤላይጃ ሙሐማድ ማልኮም “እጅግ ኃይለኛ ሆነ” በሚል ከንቅናቄው እንዲወገድ ወሰነ፡፡
ከጥቂት ሣምንታት በኋላ ታዲያ ማልኮም ኤክስ ንቅናቄውን በይፋ ለቅቆ ወደ ሜካ ሃጅ ከፈለ፡፡ እዚያ ባየውም በሙስሊሞች የዘር መሰባጠርና ብዝኅነት ልቦናው በእጅጉ መነካቱንም ተናገረ፡፡
ማልኮም ኤክስ ከሜካ “ሃጂ ማሊክ ኤል-ሻባዝ” ተብሎ ወደ ሃገሩ ተመለሰና በሰኔ 1966 ዓ.ም “የአፍሮ-አሜሪካ አንድነት ድርጅት”ን መሠረተ፡፡ ይህ ድርጅት የጥቁርን ማንነት ማስተማር፣ የአሜሪካ ጥቁሮች ጠላት የነጭ ዘር ሳይሆን ዘረኝነት መሆኑን አበርትቶ መስበክ ያዘ፡፡
ይህ የተለሳለሰ የማልኮም ፍልስፍና በሲቪል መብቶች ንቅናቄ፤ በተለይ ደግሞ በተማሪዎች ሁከት-አልባነት አስተባባሪ ኮሚቴ ዘንድ እጅግ የተወደደ እየሆነ መጣ፡፡
ማልኮም ኤክስ በኔሽን ኦፍ ኢስላም አባላት በተተኮሰ ጥይት ከመገደሉ ከአንድ ሳምንት በፊት መኖሪያ ቤቱ በቦምብ ተደብድቦ ተቃጥሏል፡፡
በማልኮም ኤክስ ግድያ ላይ መሣተፉን ያመነው ብቸኛ ሰው ታመስ ሄጋን በ1958 ዓ.ም የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶበት አርባ አራት ዓመቱን በወኅኒ ከፈፀመ በኋላ የዛሬ ሰባት ዓመት ምኅረት ተሰጥቶት ወጥቷል፡፡
በግድያው ላይ እጃቸው እንደሌለ የካዱ ከሄጋን ጋር ተፈርዶባቸው የነበሩ ሁለት ሰዎች በ1980ዎቹ ውስጥ ከእሥር ተለቅቀዋል፡፡
ማልኮም ኤክስ በአሜሪካ ጥቁሮች የሲቪል መብቶች ትግል ታሪክ ውስጥ ሲታወስ ይኖራል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5