ግማሽ ሚሊየን የሚሆኑ የሶማሊያ ስደተኞች ከሚገኙበት የኬንያው የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ኮምፕሌክስ፡፡
አንድ ለዓለምአቀፍ የረድዔት ድርጅት የሚሠራ ሹፌር ከነመኪናው ተጠልፎ የደረሰበት መጥፋቱን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡
ሁኔታውን ሲከታተል የቀየው እዚያው የሚገኘው ባልደረባችን ሄኖክ ሰማእግዜር እንደዘገበው የኬር ኢንተርናሽናል ሹፌርና የሚያሽከረክረው መኪና ማክሰኞ ዕለት የተጠለፉት ሃንዴራ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ ሲሆን ተሽከርካሪው በማግስቱ ትናንት ሶማሊያ ውስጥ በአልሻባብ ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ኪስማዩ ከተማ ውስጥ ታይቷል፡፡
ስለሁኔታው ብዙ ዝርዝር መረጃ ለጊዜው ማግኘት ባይቻልም አሽከርካሪው በሕይወት እንዳለ ተገልጿል፡፡
ዳዳብ ውስጥ ብዙዎቹ የረድዔት ድርጅቶች የሚገኙት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅጥር ግቢ ውስጥ መሆኑንና መጠለያ ጣቢያዎቹ የሚገኙባቸው አካባቢዎችና ግብረሠናይ ድርጅቶቹ የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎ በፖሊሶችና በጦር ሠራዊት አባላት እየተጠበቁ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ከመንግሥታቱ ድርጅት፣ ከዩናይትድ ስቴትስና ከሌሎችም አካላት በተጨማሪ ቱርክ፣ አልጀሪያና ቦትስዋናም እርዳታ እየሰጡ ሲሆን የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቤተሰቦችና የፊልም ተዋናይ ስካርሌት ጆሃንሰንም እዚያው ዳዳብ ይገኛሉ፡፡
ሄኖክ ከሰሎሞን ክፍሌ ጋር ያደረገውን ውይይት ያዳምጡ፡፡