“የኢትዮጵያ ተሳላሚ” የዩጋንዳ አምልኮ ቡድን አባላት ተመለሱ፤ ፓስተራቸው በሕግ እየተፈለጉ ነው

የዩጋንዳ እና ኢትዮጵያ ካርታ

በረኀብ ጽድቅን ለማግኘት፣ ከምሥራቅ ዩጋንዳ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙ፣ 80 የአምልኮ ቡድን አባላት፣ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውን፣ የዩጋንዳ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ሶሮቲ በተሰኘው የምሥራቅ ዩጋንዳ ከተማ የሚገኘው፣ “የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቤተ ክርስቲያን” አባላት፣ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት በየካቲት ወር ሲኾን፣ ፓስተራቸው፥ ከ40 ቀን ሙዓለ ጾም በኋላ፣ ኢየሱስን በኢትዮጵያ እንደሚያገኙት እንደነገራቸው፣ የዩጋንዳ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሳይመን ሙንዴይ ተናግረዋል።

የእግዚአብሔርን ዐሥርቱን ትእዛዛት ወደነበረበት መመለስ”

የገጠራማው የሶሮቲ ከተማ ነዋሪዎች የሚበዙበት የአምልኮ ቡድኑ፣ የዓለም ኅልፈት በመቃረቡ፣ ያላቸውን ንብረት እንዲሸጡ በፓስተራቸው እንደተነገራቸውም ገልጸዋል። “ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ በመተባበር ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አድርገናል፡፡ አሁን ሁሉም በሰላም ዩጋንዳ ገብተዋል፤” ያሉት ቃል አቀባዩ፣ “የአምልኮ ቡድኑ መሪው ፓስተር ሲሞን ኦፖሎት፣ ካሉበት ተይዘው ለሕግ እንዲቀርቡ፣ የደኅንነት እና የስለላ ጥምር ቡድን ተቋቁሟል፤” ብለዋል።

አማኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ከአቀኑ በኋላ፣ ኹኔታው ያሳሰባቸው የሶሮቲ ነዋሪዎች፣ ጉዳዩን ለባለሥልጣናት መጠቆማቸውን፣ ሙንዴይ አውስተዋል፡፡ የአምልኮ ቡድኑ አባላቱ፣ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የተረዱት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፣ እንደያዟቸውና የመመለሻ ሰነዳቸው እስኪዘጋጅ ድረስ፣ በአንድ ቦታ እንዳስቀመጧቸው አመልክተዋል።

እ.አ.አ. በ2000፣ “የእግዚአብሔርን ዐሥርቱን ትእዛዛት ወደነበረበት መመለስ” የሚል እንቅስቃሴ አባል የነበሩ 700 ዩጋንዳውያን፣ ራሳቸውን በማቃጠላቸው፣ በዓለም ላይ ከአምልኮ ሥርዓት ጋራ የተያያዙ እልቂቶች የከፋ ኾኖ ተመዝግቧል።