ህወሓት የታሰሩ ጋዜጠኞችን እንዲለቅቅ ሲፒጄ አሳሰበ

“የትግራይ አማፂያን የያዟቸውን አምስት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ” ሲል ሲፒጄ በሚል ምኅፃር የሚጠራው የዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ቡድን አሳሰበ።

“ከህወሓት ጋር ግንኙነት ያለው የትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሠራተኞች” ሲል ሲፒጄ የገለፃቸው አምስቱ ጋዜጠኞች የታሰሩት ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ መሆኑን ትናንት፤ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ጋዜጠኞቹ የተከሰሱት “በጦርነቱ ወቅት ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከገዥው የብልፅግና ፓርቲ ጋር በመሥራት ከጠላት ጋር ተባበብረዋል” በሚል መሆኑን ሲፒጄ ምንጮቹን ጠቅሶ በመግለጫው አመልክቷል።

“እንደ ጠላት ከተፈረጀ ማንኛውም አካል ጋር አብሮ መሥራት” የሚል ክስ እስከ ዕድሜ ልክ እሥራት ወይም እስከ ሞት የሚያደርስ ቅጣት እንደሚያከትል የጋዜጠኞች ተሟጋቹ ተቋም ጠቁሟል። “ትግራይ ውስጥ የሚሠሩ ጋዜጠኞች የፖለቲካ ዓላማ ላለው ጥቃት ዒላማ እንሆናለን ብለው ሳይሰጉ መኖርና ሥራቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ ሊፈቀድላቸው ይገባል” ብሏል ሲፔጄ።

አምስቱ ጋዜጠኞች የታሰሩት “በጦርነቱ ወቅት ትግራይ በፌዴራሉ ባለሥልጣናት ቁጥጥር ሥር በነበረች ጊዜ ሠርተዋል ለተባለ ሥራ” መሆኑን ሁለት የሲፒጄ ምንጮች መግለፃቸውን መግለጫውን የጠቀሰው ኤፍፒ ዘግቧል።

ኤኤፍፒ የህወሓት ቃል አቀባይን ምላሽ በስልክ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን አስታውቋል።

“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አስከፊ የምግብ እጥረት ባላበት ትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ፣ የግንኙነት፣ የባንክና የሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ማቋረጥን እንዲያቆሙ”ም ሲፒጄ አክሎ አሳስቧል።