ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪካ 4.8ሚሊዮን የክትባት መድሃኒቶችን ሰጠች

  • ቪኦኤ ዜና

ዩናይትድ ስቴትስ 4.8 ሚሊዮን የኮቪድ-19 የክትባት መድሃኒቶችን ለአራት አፍሪካ አገሮች መላኳን ዋይት ሀውስ ትናንት ለቪኦኤ በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡

የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት ክትባቶቹን ስርጭት የወሰነው 55 አባላት ያሉት የአፍሪካ ህብረት መሆኑን ገልጿል፡፡

በዚያ መሰረት ለቻድ 115ሺ 830፣ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ላላት ግብጽ 3 ሚሊዮን 634ሺ፣ ለጋቦን 101ሺ790፣ ለኬንያ 990ሺ 990 የፋይዘር ክትባት መድሃኒቶች መላካቸውንና ነገ አርብ ወይም ቅዳሜ እንደሚደርሱ አስታውቋል፡፡

ይህ የሆነው ዩናይትድ ስቴትስ ለራሷ የተዘጋጁ ለሁለቱም ዙሮች የሚሆኑ 33ሚሊዮን የሞደርና የኮቪድ-19 ክትባቶችን አፍሪካ ህብረት እንዲገዛው መፍቀዷን ተከትሎ ነው፡፡

የበለጸጉ አገሮች እያደረጉ ያሉት ነገር በቂ አይደለም የሚል ትችት እየቀረበ ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ ገና የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ያልወሰዱ ድሆች አገሮች እያሉ የማጠናከሪያ ክትባቶችን ትሰጣለች በሚል መተቸቷ ይታወሳል፡፡