አሜሪካውያን በየቤታቸው ነጻ የኮቪድ-19 መመርመሪያ ማዘዝ ጀመሩ

የራስ መመርመሪያ መሳሪያ

በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የኮቪድ-19 የግል መመርመሪያ በየቤታቸው በነጻ እንዲደርሳቸው የሚፈልጉ አሜሪካውያን ትዕዛዛቸውን የሚያስተላልፉበት ድረ ገጽ ከትናንት ማክሰኞ ጀምሮ መዘጋጀቱን መንግሥት አስታወቀ፡፡

https://analytics.usa.gov/የሚለው ድረ ገጽ እስከዛሬ ካሉት የመንግሥት ድረ ገጾች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የጎበኙት መሆኑም ተነግሮለታል፡፡

ድረ ገጹ የራስ መመርመሪያው መሳሪያውን በደቂቃዎች ውስጥ ማዘዝ የሚያስችል መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የራስ መመርመሪያ መሳሪያውን እሽግ በየቤቱ ለማድረስ ከ650ሺ በላይ ወንዶችና ሴቶች የፖስታ ቤት ሠራተኞች ዝግጁ ሆነዋል ሲሉም የዩናይትድ ስቴትስ ፖስታ ቤት አስተዳዳሪ ሉዊስ ደጆይ ተናግረዋል፡፡

ድረ ገጹ የተሰናዳው ፕሬዚዳንት ባይደን ባላፈው ሳምንት 500 ሚሊዮን የሚደርሱ የኮቪድ 19 የነፍስ ወከፍ መመርመሪያዎችን አስተዳደራቸው ገዝቶ የሚያቀርብ መሆኑን ባሳወቁት መሰረት መሆኑ ተገልጿል፡፡

አሜሪካውያን የመመርመሪያው መሳሪያዎቹን ከየመደብሩ ሊገዙ የሚችሉበት አማራጭ ያላቸው ቢሆንም እጥረት ያለ መሆኑን ተመልክቷል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ለጤና መድን ድርጅቶች ባስተላለፉት ትዕዛዝ የጤና መድን ላለው ሰው ሁሉ የመመርመሪያውን መሳሪያ እንዲያቀርቡ ያዘዙ ቢሆንም ድርጅቶቹ ማቅረብ የሚችሉ ቢሆንም ሂደቱ ሳምንታትን ሊፈጅ እንደሚችልና አስቸጋሪም እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡