የአፍሪካ የኮቪድ-19 አሃዝ ከተዘገበው በብዙ እጅ እንደሚበልጥ ተነገረ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ የጤና ባለሞያዋ የኮቪድ-19 ክትባት ለመስጠት እየተሰናዱ፤ ደቡብ አፍሪካ፣ እአአ ዲሴምበር 13/ 2021

በአፍሪካ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተሰራጨበትን መጠን የሚያሳዩት አሃዞች እስካሁን ከተዘገበው እና ከሚታወቀው በሰባት እጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል፤ የሟቾችም ቁጥር ከሁለት እስከ ሦስት እጅ እጥፍ በላይ ሊሆን እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ድሬክተር ተናገሩ።

"በአህጉሪቱ ያለንን የክትትል ሥርዓታችንን የሚመለከቱ ችግሮች፣ ለምሳሌም ያህል የምርመራ ቁሳቁስ አቅርቦቶች እና ሰዎች ለመመርመር ያላቸውን ዕድል ማነስ እናውቃለን" ያሉት የአህጉራዊው ፕሮግራም ድሬክተር ዶ/ር ማትሺዲሶ ሞኤቲ ትናንት ሃሙስ ይህንኑ አስመልክቶ በሰጡት ዝርዝር መግለጫ “ይሄም ጉዳዩ አቅልሎ እንዲታይ አድርጓል” ብለዋል።

የህዝብ ጤና አጠባበቅ ባለሥልጣናት በአፍሪካ ለኮሮናቫይረስ የተጋለጡ እና በዚሁም ሳቢያ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከትክክለኛው አሃዝ በእጅጉ አንሶ ሊዘገብ መቻሉን መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ ነው ያስጠነቀቁት።

የሕንድ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ በዛሬው ዕለት 58,077 አዳዲስ የኮቪድ-19 ተጋላጮችን ዘግቧል። ልክ እንደ አፍሪካ ሁሉ በህንድም የተዘገቡት የኮቪድ አሃዞች ከትክክለኛው ያነሱ ሊሆኑ መቻላቸውን አመልከተው የጤና ባለስልጣናቱ አስጠንቅቀዋል።

በሌላ የኮቪድ-19 ዜና ቁጥራቸው እስከ 3ሺህ የሚደርሱ የኒው ዮርክ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሰራተኞች የኮቪድ-19 ክትባት እንዲከተቡ የሚጠይቀውን የከተማይቱን አስተዳደር ትዕዛዝ አክብረው ካልተገኙ ከዛሬ ጀምሮ ሥራቸውን የማቋረጥ ዕጣ ሊገጥማቸው ነው።

ቀደም ሲል አንዳንድ ሠራተኞች ተቃውሞ ቢያደርጉም፣ የከተማይቱ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ ግን ከእርሳቸው በፊት በነበሩት ከንቲባ ቢል ዴብላዝዮ የተቀመጠውን ሁሉም ሰራተኞች እንዲከተቡ የሚጠይቀውን ፖሊሲ ሳያጥፉ እንዲጸና አድርገው ቀጥለዋል።

"ሰራተኞች እንዲባረሩ አናደርግም። ሥራቸውን እንዲያቆሙ ነው የምንጠይቃቸው" ነበር ያሉት አዳምስ ስለውሳኔው ሲናገሩ።

የእሳት አደጋ ተከላካይ ሰራተኞች እና የፖሊስ አባላትም ድንጋጌው ከሚመለከታቸው እና ተፈጻሚ ከሚደረግባቸው ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በፓሪስ እና በብራስልስ ባለሥልጣናት በካናዳዋ ዋና ከተማ ኦታዋ የተጀመረውን የመሰለ የረዥም ርቀት ተጓዥ ከባድ መኪኖች አሽከርካሪዎች የሚያደርጓቸውን የፀረ-ኮቪድ ህግጋት ላይ የተነጣጠሩ ተቃውሞዎች ወደ ከተሞች እንዲገቡ እንደማይፈቅዱ አስጠነቀቁ።

በፈረንሳይ ከከባድ መኪና አሽከርካሪዎቹ ተቃውሞ አድራጊዎች ከፊል ያህሉ በሳምንቱ መጨረሻ ሊያካሂዱ ላቀዱት ሰልፍ ወደ ፓሪስ በማቅናት ላይ ናቸው። በቤልጂየምም ተመሳሳይ ተቃውሞ ለፊታችን ሰኞ የካቲት 7/2014 ታቅዷል።

በሌላ በኩል የጆንስ ሆፕኪንስ የኮሮናቫይረስ መረጃ ማዕከል ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በአለም አቀፍ ደረጃ ለኮቪድ 19 የተጋለጠው ሰው ቁጥር ከ406 ሚሊዮን በላይ ሲደርስ፤ ቁጥራቸው 6 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ለህልፈት መዳርጋቸውን አመልክቷል።

በዓለም ዙሪያ እስካሁን የተሰጠው የጸረ ኮቪድ ክትባት መጠን ደግሞ ከ10 ቢሊዮን በላይ መድረሱን የማዕከሉ መረጃ ጠቁሟል።