የኮቪድ-19 ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ይዞታ

  • ቪኦኤ ዜና
ጃፓን ውስጥ የኮቪድ-19 ህሙማን ቁጥር መጨመር ተከትሎ ነዋሪዎች በከተማ እንቅስቃሴዎቻቸው የፊት መሸፈኛ ጭብል አድርገው ይዘዋወራሉ።

ጃፓን ውስጥ የኮቪድ-19 ህሙማን ቁጥር መጨመር ተከትሎ ነዋሪዎች በከተማ እንቅስቃሴዎቻቸው የፊት መሸፈኛ ጭብል አድርገው ይዘዋወራሉ።

ጃፓን ውስጥ የኮቪድ-19 ህሙማን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ሆስፒታሎች ተጨናንቀዋል። የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ዮሺሂዴ ሱጋ ሆስፒታል የሚገቡት በጽኑ የታመሙ ወይም ይጸናባቸዋል ተብሎ የሚያሰጉ የኮቪድ ህሙማን ብቻ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፥ የተቀሩት የኮቪድ ህሙማን በቂ የሆስፒታል ቦታ እስከሚገኝ ቤታቸው ራሳቸውን ለይተው መቆየት አለባቸው ብለዋል። ጃፓን ውስጥ በየቀኑ አስር ሺህ የኮቪድ ተጋላጮች የሚገኙ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ የሃገሪቱ ብሄራዊ የህክምና ባለሙያዎች ማህበር አስቸኳይ ጊዜ እንዲታወጅ ጠይቋል።

ቻይና ውስጥ ደግሞ የዉሃን ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲያካሂዱ ትዕዛዝ ተሰጠ። ትዕዛዙ የተሰጠው በከተማዋ ከአንድ ዓመት በኋላ የመጀመሪያ በሃገር ውስጥ ለቫይረሱ የተጋለጠ ሰው ከተገኘ በኋላ መሆኑ ታውቋል።

አስራ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ያላት ዉሃን እአአ በ2019 የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ተያዥ ከተገኘ በኋላ ነዋሪዎቹ በጠቅላላ ለሰባ ስድስት ቀናት በጥብቅ ቁጥጥር ከቤት እንዳይወጡ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል።

ዴልታ የተባለው የኮሮናቫይረስ ዝርያ መዛመት ስጋት ውስጥ የከተታቸው ሃገሮች ቁጥር ጨምሯል። ደቡብ ኮሪያ የዚሁ የዴልታው ቫይረስ ተቀጥላ ዝሪያ የሆነ ዴልታ ፕለስ የተባለው ዐይነት ሁለት ዜጎቼን ይዞብኛል ስትል አስታውቃለች።

ቀደም ብለው ብሪታንያ ህንድ እና ፖርቱጋልን ጨምሮ የተለያዩ ሃገሮች በዚሁ ዴልታ ፕለስ በሚባለው ዐይነት የተያዙ ጥቂት ሰዎች ማግኘታቸውን ገልጸው ነበር።

የዓለም የጤና ድርጅትም በክትባቱ ያለመበገር ባህሪ ሊፈጥር ስለሚችል የቫይረሱን መለዋወጥ በቅርበት መከታተል እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

በዴልታ ዝርያው ሳቢያ የኮሮናቫይረስ ተያዞች ቁጥር እየበዛ ባለበት የዩናይትድ ስቴትስ ሰራተኞቻቸው የኮቪድ-19 ክትባት መከተብ ያለባቸው መሆኑን አለዚያ በየጊዜው እንዲመረመሩ መመሪያ የሚሰጡት አስተዳደሮች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

የኮሎራዶ ዴንቨር ከተማ ከንቲባ ማይክል ሃንኮክ የከተማዋ አስተዳደር ሰራተኞች እና ተጋላጭ የሆኑ የግል ተቋማት ሰራተኞች እስከ መጪው መስከረም መጨረሻ ድረስ እንዲከተቡ ትዕዛዝ እንደሚወጣ ትናንት አስታውቀዋል።

የኒው ጀርዚ አገረ ገዢ ፊል መርፊ በበኩላቸው የክፍለ ሃገርዋ የጤና ሰራተኞች፥ በማረሚያ ቤቶች እና በአረጋውያን እና ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች መኖሪያ ማዕከሎች የሚሰሩትም በሙሉ እንዲከተቡ አለዚያ በሳምንት ሁለት ጊዜ መመርመር እንዳለባቸው አስታውቀዋል። የአጎራባቿ ኒው ዮርክ አገረ ገዢ አንድሩው ኮሞ በበኩላቸው የንግድ ድርጅቶች ያልተከተቡ ደንበኞችን አንቀበልም እንዲሉ አሳስበዋል። ተገልጋዮቻችሁ ጎናቸው የተቀመጠው ሰው የተከተበ ሰው መሆኑን ማውቅ ስለሚፈልጉ ለድርጅታችሁ ጥቅም ስትሉ ያን ማድረግ አለባችሁ ብለዋል አገረ ገዢ ኮሞ።

በሌላ ዜና በዩናይትድ ሴቴትስ የመወሰኛ ምክር ቤት የደቡብ ካሮላይና ክፍለ ግዛት ሪፐብሊካን ሴኔተር ሊንዚ ግራም ኮሮናቫይረስ እንደያዛቸው ተገልጿል። የኮቪድ ክትባት ከተከተቡ በኋላ ቫይረሱ እንደያዛቸው ያስታወቁ የመጀመሪያ የዩናይትድ ስቴትስ ሴኔተር ሲሆኑ ትናንት ባወጡት መግለጫ

ፎቶ ፋይል፦ በዩናይትድ ሴቴትስ የመወሰኛ ምክር ቤት የደቡብ ካሮላይና ክፍለ ግዛት ሪፐብሊካን ሴኔተር ሊንዚ ግራም

ፎቶ ፋይል፦ በዩናይትድ ሴቴትስ የመወሰኛ ምክር ቤት የደቡብ ካሮላይና ክፍለ ግዛት ሪፐብሊካን ሴኔተር ሊንዚ ግራም

"ቅዳሜ ዕለት እንደጉንፋን አድርጎ ጀማመረኝ እና ዶክተሬ ዘንድ ዛሬ ሄጄ ነው ቫየረሱ እንደያዘኝ የታውቀው። አሁን የህመም ስሜቴ ቀለል ያለ ነው። ለአስር ቀን ያህል ራሴን አግልዬ እቆያለሁ" ብለዋል።

የስድሳ ስድስት ዓመቱ ሴኔተር ግራም የኮቪድ ክትባት ባለፈው ታህሳስ መከተባቸውን አስታውቀዋል።

በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ሲዲሲ አሻሽሎ ባወጣውም መምሪያ ዴልታው የቫይረሱ ዝርያ እየተዛመተ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሰዎችም ጭምር ቫይረሱ በብዛት እየተዛመተ ባለባቸው አካባቢዎች ዝግ በሆኑ ስፍራዎች የአፍና አፍንጫ ጭንብል ማድረግ እንዲቀጥሉ አሳስቧል።