ኮቪድ-19 በዓለም

  • ቪኦኤ ዜና

ብሪታንያ ውስጥ በዓለም አቀፉ ኮቪድ-19 ምክንያት ጥለው የቆዩት የእንቅስቃሴ ክልከላዎች መነሳታቸው በተጨማሪ ሁለት ወይም አራት ሳምንት እንደሚራዘም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ዛሬ ያስታውቃሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

የእንቅስቃሴ ክልከላዎቹ መነሳት ለመዘግየቱ ምክንያት የሆነው ህንድ ውስጥ የተቀሰቀሰው ዴልታ የኮሮናቫይረስ ዝርያ እንግሊዝ ውስጥ እየጨመረ መምጣቱ መሆኑን ተገልጿል።

ዚምባቡዌም የኮሮናቫይረስ ሥርጭቱን ለመቆጣጠር የእንቅስቃሴ ክልከላዎቹን መልሳ ለማጽናት ወስናለች። የዚምባቡዌ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ በቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ ሰው አስፈላጊዎቹን የጥንቃቄ እርምጃዎች ተግባራዊ ማደረጉ ላይ ችላ ማለቱ ቫይረሱ በይበልጥ እንዲዛመት አድርጓል ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ደግሞ ቴክሳስ ክፍለ ሃገር ውስጥ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል ለሰራተኞቹ የኮቪድ-19 ክትባት መውሰድን ግዴታ ማድረጉን በተመለከተ በፍርድ ቤት የቀረበውን ሙግት ዳኛው ውድቅ አድርገውታል።

ጉዳዩ ላይ ያስቻሉት ዳኛ ሊን ሂዩስ የሂዩስተን ሜተዲስት ሆስፒታል ሰራተኞች የክትባት ምርምር ላይ እየተሳተፉ አይደለም፥ ሆስፒታሉ ታካሚዎቹን ራሱ ለቫይረሱ ሳያጋልጥ ህይወታቸውን ለማትረፍ እየሰራ ነው፣ የክትባቱም ጉዳይ ሰራተኞቹን ታካሚዎቹን እና የታካሚ ቤተሰቦችን ደኅንነት ያስጠብቅልኛል ያለው አማራጭ ነው በማለት ክሱን ውድቅ አድርገዋል።