ኮቪድ-19 በዓለም

  • ቪኦኤ ዜና

በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ከ9.4ሚሊዮን ያለፈ ሲሆን በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ4መቶ 83ሺህ አልፏል።

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የቫይረሱ ተጠቂዎች አሃዝ በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ 10ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል አስገንዝበዋል።

ይህ የቫይረሱ ሥርጭት ማሻቀብ ትንበያ የሚነግረን መከላከያውን ክትባት እና መድሃኒት ለማግኘት ምርመሩን እየቀጠልን ቫይረሱን መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ የማድረግ ጊዜ የማይሰጥ ኃላፊነት ያለብን መሆኑን ነው ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ አጥብቀው አሳስበዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ በቫይረሱ በተጠቁ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚነቷ እንደቀጠለ ሲሆን ቁጥሩ በአሁኑ ወቅት ከ2.3 ሚሊዮን አልፏ፤ እስከዛሬ ማለዳ ድረስ ህይወታቸውን ያጡት ከ1መቶ 22ሺህ በልጧል።

ቀደም ብሎ በወረርሽኙ የተጠቃችው የኒው ዮርክ ክፍለ ግዛት ባለፉት ሳምንታት የቫይረሱ መዛመት ካሻቀበባቸው ክፍለ ግዛቶች የሚገቡ ተጓዦችን ለሁለት ሳምንት ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ አዛለች።

የኒው ዮርክ አገረ ገዥ አንድሩው ኮሞ ትናንት ይፋ ያደረጉት ትዕዛዝ ፎሎሪዳ አሪዞና ቴክሳስ ሰሜን እና ደቡብ ካሮላይና አላባማ እና ዩታህን ይመለከታል፤

አንድሩው ኮሞ የለይቶ ማቆያ ትዕዛዙን መግለጫ ሲሰጡ አብረዋቸው የነበሩት የአጎራባች ኒው ጀርዚ እና ከኔቲከት ክፍለ ግዛቶች ሃገረ ገዢዎችም ተመሳሳይ እርምጃ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።