ሀማስ እአአ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ሰባት ቀን በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ለማሰብ፣ ዛሬ ሰኞ በዓለም ዙሪያ የመታሰቢያ ሥነ-ስርዓቶች ተካሂደዋል። የዓለም መሪዎችም ፀረ-ሴማዊነት እንዲያበቃ እና የእስራኤል ታጋቾች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
ባለፈው ዓመት የአይሁድ በዓል ክብረ በዓል 1ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን የገደለው ድንገተኛ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት የእስራኤልን የጸጥታ ስጋት ያባባሰ ሲሆን፣ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ስጋት ውስጥ የነበሩ ሀገራት በመካከለኛው ጦርነት ሌላ ጦርነት እንዲጋፈጡ ሆነዋል።
የሀማስን ጥቃት እና እሱን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በከፈተችው ጦርነት 41 ሺህ ሰዎች መገደላቸውን እና ከ1.9 ሚሊየን በላይ ተከትሎ በአውሮፓ የሚኖሩ በርካታ የአይሁድ እና የሙስሊም ማኅበረሰቦችም ፀረ-ሴማዊ እና ፀረ-ሙስሊም ስሜቶችን ለማርገብ ሲጥሩ ቆይተዋል።
በበርሊን የጀርመን ቻንስለር ፅህፈት በሐማስ የታገቱትን እስራኤላውያን ለመዘከር በቢጫ ሪቫን ያጌጠ ሲሆን በጥቃቱ የተገደሉ እና የታገቱ ሰዎች ስም በብራንደንበርግ ሐውልት መግቢያ ፊት ለፊት ተነቧል። የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክክት "ሀማስ በእስራኤል ላይ ባደረሰው አስከፊ ጥቃት በፍልስጤም ህዝብ ላይም ውድመት አስከትሏል" ብለዋል። በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግና ጦርነቱ በመካከለኛው ምስራቅ እንዳይስፋፋ ዓለም አቀፍ ጥረት እንዲደረግም ጠይቀዋል።
በተመሳሳይ ለእስራኤል ጠንካራ ድጋፍ የሰጡት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ የጥቅምት ሰባትን መታሰቢያ ሮም የሚገኘውን ምኩራብ በመጎብኘት እና እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት በማረጋገጥ ዕለቱን አስበዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው የሀማስን ጥቃት አንደኛ ዓመት አስመልክቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ባስተላለፉት መልዕክት "ከአመት በፊት የተሰማን የህመም ስሜት አሁንም ድረስ አለ። የእስራኤል ህዝብ ህመም፣ የእኛም፣ የቆሰለው የሰው ልጅ ህመም ነው" ብለዋል። ጥቃቱ የደረሰባቸው፣ ታጋቾችን እና እና ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያስቡ በመግለፅም ኤክስ በተሰኘው የትስስር ገጻቸው ፅፈዋል።