የአሜሪካ ምክር ቤት በቻይና ላይ ያነጣጠሩ ረቂቅ ሕጎችን ሊመለከት ነው

የብሪታንያ ወታደሮች በፎርት ኢርዊን ካሊፍ በፕሮጀክት ኮንቬርጀንስ ልምምዶች ወቅት ሰው አልባ አውሮፕላን ሲያጀመሩ

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከበጋ ወራት እረፍት መልስ ምክር ቤት የቻይናን ተፅእኖ እና ኃይል ለመግታት እና ለመመከት የሚያስችሉ ረቂቅ ህጎችን ዋና ትኩረታቸው እንደሚያደርጉ ተገልጿል። ሕግ አውጪዎች በቤይጂንግ የባዮቴክኖሎጂ፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) እና የኤሌክትሪክ መኪናዎች ላይ ያነጣጠሩ ረቂቆችን ማዘጋጀታቸውም ተመልክቷል።

ዋሽንግተን ቤይጂንግን እንደ ትልቅ ጂኦፖለቲካዊ ተቀናቃኝዋ የምትመለከታት ሲሆን የተዘጋጁት ሕጎች አሜሪካ በፉክክሩ አሸናፊ ሆና መውጣቷን የሚያረጋግጡ እንደሚሆኑ ተነግሮላቸዋል። በዚህ ሳምንት ድምጽ ሊሰጥባቸው የታቀዱት አብዛኞቹ ረቂቅ ህጎችም የሪፐብሊካን እና የዲሞክራቶችን ድጋፍ ያገኙ መሆናቸውም ተገልጿል።

በአሜሪካ ምክርቤት የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ጉዳይ ልዩ ኮሚቴ ሊቀመንበሩ የሚሺጋኑ ሪፐብሊካን የምክር ቤት አባል ጆን ሙሌናር፣ ረቂቅ ሕጎቹ "የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የደቀነውን ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ርዕዮተ ዓለማዊ ስጋት ለመመከት ትርጉም ያለው እርምጃ ይወስዳሉ" ብለዋል።

የመብት ተሟጋች ቡድኖች ረቂቅ ሕጎቹ በእስያ አሜሪካውያን ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጉዳት በመጥቀስ ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በበኩሉ ረቂቅ ህጉ “የተለየ አስተሳሰብን ለመጨፍለቅ የሚደረግ ኢፍትሃዊ ዘመቻ ነው” ብሏል። የኤምባሲው ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ፣ ረቂቅ ሕጉ ከፀደቀ በቻይና እና አሜሪካ ግንኙነት እና የጋራ ጥቅም ላይ ጣልቃ እንደሚገባ እና የአሜሪካን ጥቅም፣ አንድምታ እና ተዓማኒነት እንደሚጎዳም ተናግሯል።