የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የመንግሥቱን በጀት ነገ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ማይክ ጆንሰን

በዩናይትድ ስቴትስ ነገ ዓርብ እኩለ ሌሊት ላይ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በበጀት እጦት ከመዘጋጀታቸው በፊት፣ ምክር ቤቱ የ1.2 ትሪሊየን ዶላር በጀት ለማጽደቅ ሩጫ ላይ ነው።

በሁለቱም ፓርቲዎች ስምምነት ላይ የተደረሰበትና ዛሬ ሌሊት የቀረበውን የ1.2 ትሪሊየን ዶላር በጀት፣ በሪፐብሊካን ቁጥጥር ሥር ያለው የተወካዮች ም/ቤት ነገ ዓርብ ድምጽ እንደሚሰጥበት የሚጠበቅ ሲሆን፣ በመቀጠል ደግሞ በዲሞክራቶቹ የበላይነት ለተያዘው የሕግ መወሰኛ ም/ቤት ወይም ሴኔት እንደሚቀርብ ይጠበቃል። የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ሕጉን ተወያይቶ ለማጽደቅ የሚኖረው የተወሰኑ ሰዓታት ብቻ ነው።

ስድስት ረቂቅ ሕጎችን የያዘው የበጀት ዕቅድ በሁለቱም ፓርቲዎች እንዲሁም በተወካዮች ም/ቤቱ እና በሴኔቱ ስምምነትና ሰጥቶ መቀበል ድርድር የተደረሰበት መሆኑን ከሁለቱም ፓርቲዎች የተውጣጡ መሪ ተደራዳሪዎች አስታውቀዋል።

በጀቱ መጽደቅ የነበረበት ከስድስት ወራት በፊት ባለፈው ጥቅምት ወር ነበር። ላለፉት ስድስት ወራት የአሜሪካ ኮንግረስ የተወሰኑ ሳምንታት ወጪዎችን የሚሸፍን የተወሰነ ገንዝብ በመልቀቅ የመንግሥት ሥራ እንዲቀጥል ሲያደርግ ሰንብቷል። ነገ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው በጀት ለቀሪዎቹ ስድስት ወራት የሚያገለግልና ቀሪውን የበጀት ዓመት የሚሸፍን እንደሆነ ታውቋል።

ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ከሠሩ፣ የመንግሥት መ/ቤቶችን ከመዘጋት ማዳን እንደሚችሉ፣ በሴኔቱ የአብላጫው ፓርቲ የሆነው የዲሞክራቲክ ፓርቲው መሪ ቻክ ሹመር ተስፋቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካ ዕዳ በመጪዎቹ ሠላሳ ዓመታት በእጅጉ እንደሚጨምር፣ አሁን ያለው 34.5 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳ የአገሪቱን አጠቃላይ ምርት 99 በመቶ እንደሚያህል፣ እ.አ.አ በ2054 ዕዳው የአጠቃላይ ምርቱን 166 በመቶ የሚያህል እንደሚሆን፣ በአሜሪካ ኮንግረስ የሚገኘው የበጀት ቢሮ አስጠንቅቋል።