ላለፉት ሦስት ቀናት ምዕራብ ሩዋንዳ ውስጥ በሚገኘው የዓለሙ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ደጃፍ ከትመው ያሳለፉ ስደተኞችን ለመበተን የሀገሪቱ ፖሊስና ጦር ሠራዊት አባላት ዛሬ በወሰዱት እርምጃ አምስት የኮንጎ ዜጎች ተገድለዋል። ሕይወት ያለፈው ጥይት በመጠቀማቸው መሆኑ ተዘግቧል።
ዋሺንግተን ዲሲ —
ላለፉት ሦስት ቀናት ምዕራብ ሩዋንዳ ውስጥ በሚገኘው የዓለሙ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ደጃፍ ከትመው ያሳለፉ ስደተኞችን ለመበተን የሀገሪቱ ፖሊስና ጦር ሠራዊት አባላት ዛሬ በወሰዱት እርምጃ አምስት የኮንጎ ዜጎች ተገድለዋል። ሕይወት ያለፈው ጥይት በመጠቀማቸው መሆኑ ተዘግቧል።
የሩዋንዳ ፖሊስ ያወጣው መግለጫ፣ በዚህ “ሃያ ረባሽ” ሲል የጠራቸው ስደተኞች እና 7 ፖሊሶች በተጎዱበት ድንገት ተመጣጣኝ ኃይል ተጠቅመናል ይላል። ሁሉም በፍጥነት ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውንና አምስቱ ስደተኞች ግን ሕይወታቸው ማለፉንም የፖሊሱ መግለጫ አክሏል። የሟቾቹ ቁጥር ፖሊስ ከሰጠው ሊበልጥ እንደሚችል ስደተኞቹ ተናግረዋል።
ፖሊስ ሕገወጥ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፣ ጠለፋና ሁከት ለመቀስቀስ ሞክረዋል ሲል የከሰሳቸውን 15 ስደተኞች ማሠሩንም ጨምሮ አስታውቋል።
በሩዋንዳ ካሮንጊ አውራጃ ውስጥ በሚገኘው ካምፕ ብቻ ከ17 ሺሕ በላይ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ስደተኞች ተጠልለው ይገኛሉ። ስደተኞቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ ተቃውሞ የሚያሰሙት፣ የምግብ ራሺኑ 25 በመቶ መቀነሱን ነው።