ባለፈው ሳምንት በኮንጎ የተካሄድውን ምርጫ የተከታተሉ ታዛቢዎች፣ በምርጫው ሂደት በርካታ የህግ ጥሰቶች ታይተዋል ማለታቸውን ተከትሎ፣ አወዛጋቢ የምርጫ ውጤቶች በተመዘገቡባቸው አካባቢዎች ምርጫው እንዲደገም ተቃዋሚዎች ያቀረረቡትን ጥያቄ የሀገሪቱ መንግስት ውድቅ አድርጓል።
ታህሳስ 10 በተካሄደው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ እስካሁን ይፋ የተደረጉ ውጤቶች ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ እየመሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ቢሆንም፣ በድምፅ አሰጣጥ እና አፈፃፀም ዙሪያ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የሚገልፁት ተቃዋሚዎች ውጤቱ እንዲሰረዝ ጠይቀዋል። ይህ ውዝግብ፣ በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር የምትናወጠውን ኮንጎ የበለጠ ወደ አለመረጋጋት እንዳያመራት ተሰግቷል።
የፕሬዝዳንት እና ምክርቤት አባላትን ምርጫ በዋናነት የታዘበው፣ ገለልተኛ የኮንጎ ካቶሊክ እና ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያናት ጥምረት ባወጣው አዲስ ሪፖርት፣ በተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የተከሰቱ 5 ሺህ 42 ጥሰቶች ሪፖርት እንደደረሰው አስታውቋል። ከነዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት የድምፅ አሰጣት ሂደቱን ያስተጓጎሉ ነበሩም ብሏል።
ቡድኑ አክሎ "የህግ ጥሰቶቹ በምርጫ ውጤቶቹ ላይ ተፅእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ" ሲል አመልክቷል።
ምርጫውን ያስተባበረው የሀገሪቱ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ኮሚሽን አጠቃላይ ውጤቱን በተቀመጠለት ቀነ ገደብ መሰረት እ.አ.አ ታህሳስ 31 ይፋ እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን፣ እስካሁን በተሰበስሰበው ውጤት ፕሬዝዳንት ሼሴኬዲ ከ18 ተወዳዳሪዎቻቸው በልጠው እየመሩ መሆናቸውን ያሳያል።
ኮምሽኑ ድምፅ ከተሰጠባቸው 75ሺህ 969 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ እስካሁን ይፋ ማድረግ የቻለው፣ ከ46ሺህ 422 ጣቢያዎች የተገኙ ውጤቶችን ብቻ መሆኑም ተገልጿል።