ኮንጎ የመጀመሪያዋን ሴት ጠቅላይ ሚንስትር ሰየመች

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ የኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሼኬዲ

የኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሼኬዲ ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆኑትን ሴት ጠቅላይ ሚንስትር መሾማቸው ተገለጠ። ፕሬዚደንቱ የቀድሞ የፕላን ሚንስትር የነበሩትን ጁዲት ሱሚንዋ ቱሉካን ትናንት ሰኞ ጠቅላይ ሚንስትር አድርገው ሾመዋቸዋል።

ባለፈው የአውሮፓውያኑ 2023 በድጋሚ የተመረጡት እና አዲሱን መንግሥታቸውን በማዋቀር ላይ ያሉት ፕሬዚደንት ቲሼኬዲ፡ ሴት ጠቅላይ ሚንስትር በመሾም በምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረጋቸውን ዘገባው አውስቷል።

አዲሷ ጠቅላይ ሚንስትር ኃላፊነቱን የሚረከቡት በማዕድን በከበረው እና ከሩዋንዳ ጋር በሚዋስነው በምስራቁ የሃገሪቱ ክፍል ሁከቱ እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት ነው። አዲሷ ጠቅላይ ሚንስትር ጁዲት ሱሚንዋ ቱሉካ ሹመታቸውን ተከትሎ በመንግሥቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ ባሰሙት የመጀመሪያ ንግግራቸው፣ ለኮንጎ ሰላም እና ልማት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። ሆኖም ሂደቱ በሀገሪቱ ካሉት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ብርቱ ድርድር ማድረግ ስለሚጠይቅ አዲስ መንግሥት ለማቋቋም በርካታ ወራት ሊወስድ እንደሚችልም ተመልክቷል።