በታላቋ ብሪታንያ ንግሥት ዳግማዊት ኤልሣቤጥ የሚመራው የጋራ ብልፅግና ሃገሮች መሪዎች ጉባዔ ለንደን ላይ እየተካሄደ ነው።
ዋሺንግተን ዲሲ —
በታላቋ ብሪታንያ ንግሥት ዳግማዊት ኤልሣቤጥ የሚመራው የጋራ ብልፅግና ሃገሮች መሪዎች ጉባዔ ለንደን ላይ እየተካሄደ ነው።
በዛሬው ጉባዔ ላይ የጋራ ብልፅግና ኅብረቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚመለከቱ ሃሣቦች የተንፀባረቁ ሲሆን የድርጅቱን አስፈላጊነትና የቀድሞዪቱ ገዥ ብሪታንያ ልትጫወት ስለምትችለው ሚና በውይይቱ ላይ የተነሱ ጥያቄዎች መሆናቸው ታውቋል።
ጉባዔው ሲከፈት ግርማዊትነታቸው ባደረጉት ንግግር የጋራ ብልፅግናው አመራር ወደፊትም በእርሣቸው ቤተሰብ እጅ ውስጥ እንዲቆይ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።
የጋራ ብልፅግናው ማኅበር “ለመጭ ትውልዶችም መረጋጋትና ቀጣይነትን እንዲያበረክት ከልቤ እመኛለሁ፤ አንድ ቀን የዌልስ ልዑልም ኅብረቶቻችንንና ሥራዎቻችንን ከፍ በማድረግና በማጠናከር የእኔ አባት በ1949 ዓ.ም. ጀምረውት የነበረውን እጅግ ጠቃሚ ተግባር እንዲቀጥል ለማድረግ እወስናለሁ፤ ” ብለዋል ንግሥት ኤልሣቤጥ በኪንግሃም ቤተመንግሥት ውስጥ ለተሰበሰጡት መሪዎች።
ኮመንዌልስ ወይም የጋራ ብልፅግናው ማኅበር የተመሠረተው በዓለም ላይ ተንሠራፍቶ የነበረው የታላቋ ብሪያንያ ንጉሠ-ነገሥታዊ ቅኝ አገዛዝ ሲፈራርስ ሲሆን ዛሬ 53 አባል መንግሥታት ያሉት የወደፊት ሕልውናው እያንገራገረ እንደሆነ የሚታማ ድርጅት ነው።