በድጋሚ የታደሰ
የዩናይትድ ስቴትስ ኮሎራዶ ግዛት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዚደንት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በክፍለ ግዛቱ ፕሬዚዳንታዊ ቅድመ ምርጫ መቅረብ አይችሉም” ብሎ ውሳኔ ሰጠ፡፡
ሌሎችም ክፍለ ግዛቶች የቀድሞው ፕሬዚደንት በድጋሚ ለመመረጥ እንዳይወዳደሩ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ባሉበት በዚህ ወቅት የኮሎራዶው ፍርድ ቤት ውሳኔ ትልቅ ትኩረት ስቧል፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን የሰጠው የዩናይትድ ስቴትስ ህገ መንግሥት “በአመጽ ወይም በነውጥ የተሳተፉ ግለሰቦች የመንግሥት ሥልጣን እንዳይዙ የሚደነግገውን 14ኛው የማሻሻያ አንቀጽ በመጥቀስ ነው፡፡
እአአ እስከ መጪው ጥር 4 ቀን ወይም የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ የውሳኔው ተፈጻሚነት በይደር እንደሚያዝ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ የኮሎራዶ ባለስልጣናት የቅድመ ምርጫው ድምጽ መስጫ ካርዶች ታትመው የሚወጡበት የመጨረሻ ቀን ጥር 5 እንደሚሆን አሳውቀዋል፡፡
የኮሎራዶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቀውን ውሳኔ ያሳለፈው በ4 ለ3 የድምጽ ብልጫ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ለደረሰበት ውሳኔ መሰረት የሆነው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዶናልድ ትረምፕን ያሸነፉበትን ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት ለመቀልበስ እኤአ ጥር 6 2021 ዓም በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ላይ የተካሄደው አመጽ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
“በአመጹ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ትረምፕ የነበራቸው ሚና ለፕሬዚዳንትነት በሚደረገው የምርጫ ውድድር እንዳይሳተፉ ያደርጋቸዋል” የሚል ክርክር ተነስቷል፡፡
ትረምፕ በቅድመ ምርጫው እንዳይቀርቡ የወሰኑባቸው ዳኞች “በቀላሉ የደረስንበት ውሳኔ አይደለም፡፡ የጉዳዩን ክብደት እና ጥያቄዎች እንደሚመጡ እንረዳለን፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ ሳንፈራ እና ሳናዳላ፡ ውሳኔያችን በሚያስከትለው ምላሽ ምክንያትም ሳናወላውል ህጉን ተግባራዊ ልናደርግ ቃለ መሐላም መፈጸማችንን እናውቃለን” ብለዋል፡፡
ውሳኔውን ተቃውመው ድምጽ የሰጡት ዳኛ ካርሎስ ሳሙር በበኩላቸው “መንግሥት ካለተገቢው ህጋዊ ሂደት ግለሰቦችን በህዝብ እንዳይመረጡ ለመከልከል አይችልም” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
ዶናልድ ትረምፕ በጆ ባይደን የተሸነፉበት የፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት ለማስቀልበስ ሴራ አቀነባብረዋል በሚል የቀረቡባቸውን ክሶች አስተባብለዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚደንት ምርጫ ዘመቻ የኮሎራዶ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ “እጅግ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ” ሲል አጣጥሎ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ጉዳያችንን ተመልክቶ በፍጥነት እንደሚፈርድልን እና እነዚህን ከአሜሪካዊነት ውጪ የሆኑ ክሶች ያስቆምልናል ብለን እንጠብቃለን” ብሏል፡፡