ድንበር አቋርጠው ወደ አሜሪካ የሚገቡ ቻይናውያን ቁጥር በመጨመር ላይ ነው

  • ቪኦኤ ዜና
ድንበር አቋርጠው ወደ አሜሪካ የሚገቡ ቻይናውያን ቁጥር በመጨመር ላይ ነው

ድንበር አቋርጠው ወደ አሜሪካ የሚገቡ ቻይናውያን ቁጥር በመጨመር ላይ ነው

በአሜሪካ ደቡብ ድንበር በኩል የሚገቡ የቻይና ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አክሲዮስ የተሰኘው የዜና አገልግሎት ዘግቧል። ጭማሪው የታየው ቻይና በምትከተለው የኮቪድ ፖሊሲ ምክንያት እንዲሁም አገሪቱ ድንበሯን ክፍት በማድረጓ ነው ተብሏል። ወደ አሜሪካ በደቡብ ድንበር በኩል የሚገቡት ቻይናውያን ቁጥር ባለፈው አንድ ዓመት በአስር እጥፍ መጨመሩ ታውቋል። ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ 4ሺሕ 366 ቻይናውያን ድንበሩን አቋርጠው በህገ ወጥ መንገድ ገብተዋል።

ኢኳዶር የቻይና ዜጎችን ካለ ቪዛ መቀበሏ ለስደተኞቹ መምጣት አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ 3ሺሕ የሚሆኑ ስደተኞች ከደቡብ ሜክሲኮ በመነሳት 750 ኪሜ የሚፈጀውንና ወደ መዲናዋ ሜክሲኮ ሲቲ የሚያደርጉትን የእግር ጉዞ ጀምረዋል። ተስፋቸው አሜሪካ ድንበር መድረስ ነው።

ስደተኞቹ ረጅም ግዜ በሚወስደው ቪዛ ተሰላችተው በተቃውሞ የእግር ጉዞውን መጀመራቸው ታውቋል። በቡድን የሚደረገው ጉዙ ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ በተቃውሞ የሚደረግ ሲሆን ባለፈው ረቡዕ አንድ የስደተኞች መብት አቀንቃኝ እና ስድስት ፍልሰተኞች ከንፈራቸውን በክር በመስፋት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። አንድ ላይ ሆኖ በቡድን መጓዙን የሚመርጡት ከህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎችና ከሌሎችም ከሚደርሥባቸው ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ነው ተብሏል።