ለታይዋን የጦር መሣሪያዎች እንዲሸጡ ድጋፍ ያደርጋሉ በሚል ቻይና ሁለት የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች፡፡
በጦር መሣሪያዎች ምርት ላይ የተሠማሩት ሁለቱ ኩባንያዎች፣ ‘ጀኔራል አቶሚክስ ኤሮኖቲካል ሲስተመስ’ እና ‘ጀኔራል ዳይናሚክስ ላንድ ሲስተምስ’ በቻይና ያላቸው ገንዘብና ንብረት የታገደ ሲሆን፣ የሥራ ኃላፊዎቻቸውም ወደ ሃገሪቱ እንዳይገቡ ታግደዋል።
ጀኔራል ዳይናሚክስ ግማሽ ደርዘን የሚሆኑና ‘ገልፍስትሪም’ የተሰኙ አውሮፕላኖችን እንዲሁም የጄቶችን አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ ጀኔራል አቶሚክስ የተሰኘው ኩባንያ ደግሞ ‘ፕሪዴተር’ እና ‘ሪፐር’ የተሰኙ በአሜሪካ ጦር ጥቅም ላይ የዋሉ ድሮኖችን እንደሚያመርት ታውቋል። ጀኔራል ዳይናሚክስ ‘ኤብራም’ የተሰኙና ለታይዋን የተሸጡ ታንኮችን እንደሚያመርት ተመልክቷል።
ቤጂንግ ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ማዕቀቦችን እንደምትጥል ስታስጠነቀቅ የነበረ ቢሆንም፣ ኮቪድ 19 በኢኮኖሚው ላይ ባደረሰው ጉዳት፣ ከፍተኛ የሥራ አጥነት እንዲሁም ከውጪ የሚገባው መዋዕለ ነዋይ በመሳሳቱ ተግባራዊ ሳታደርግ ቀርታለች፡፡