የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሰሜን ኮሪያ፣ በሆንግ ኮንግ የሚገኘውን ቆንስላ ጄነራል ለመዝጋት ያሳለፈችውን ውሳኔ እንደሚያከብር፣ ዛሬ ረቡዕ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ሰሜን ኮሪያ፣ በስፔይንና በአፍሪካ ሀገራት ያሏትን ጨምሮ በርካታ ኤምባሲዎቿን ለመዝጋት እንደተዘጋጀች፣ የብዙኀን መገናኛ ዘገባዎች እና ተንታኞች ገልጸዋል።
በዚኽ ርምጃዋም፣ በመላው ዓለም ከሚገኙ ሚሲዮኖቿ፣ 25 በመቶዎቹ ሊዘጉ እንደሚችሉ ተመልክቷል፡፡
ይህም፣ ወትሮም ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ የተነጠለችው ሰሜን ኮሪያ፣ በተጣሉባት ማዕቀቦች፣ ከባሕር ማዶ ገንዘብ ለማግኘት እየተቸገረች እንደኾነ ያሳያል፤ ሲል፣ የደቡብ ኮሪያ የትስስር ሚኒስቴር፣ ትላንት ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ሰሜን ኮሪያ፣ ከ159 የዓለም ሀገራት ጋራ መደበኛ ግንኙነት አላት፡፡ በአሁኑ ወቅት፣ 53 የባሕር ማዶ የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖቿ የነበሯት ሲኾን፣ ከእኒኽም ውስጥ፣ ሦስቱ ቆንስላዎች እና ሦስቱ ደግሞ የተወካይ ጽሕፈት ቤቶች ብቻ እንደኾኑ፣ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡