ዋሺንግተን ዲሲ —
የቻይና ብሄራዊ የጤና ኮምሽነር ምክትል ሚንስትሩ ዜንግ ዪክሲን የዓለም የጤና ድርጅት የኮቪድ-19ን አነሳስ በተመለከተ ሁለተኛ ምዕራፍ ጥናት ለማካሄድ ማቀዱ በጣም አሳዝኖናል ብለው ኮሮናቫይረስ የተዛመተው ከቻይና ቤተ ሙከራ አምልጦ ነው የሚባለው መላ ምት ከዕውነታ የራቀ ነው ሲሉ አጣጥለዋል።
ባለፈው ሳምንት የዓለም የጤና ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ዓለም አቀፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከቻይና ቤተ ሙከራ ካመለጠ ቫይረስ ጋር ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም የሚለውን መላ ምት ከወዲሁ ትክክል አይደለም ብሎ መደምደም እንደማይቻል ተቀብለዋል።
የቻይናው ከፍተኛ የጤና ጥበቃ ባለስልጣን ዤንግ በበኩላቸው ዉሃን በሚገኘው ቤተ ሙከራ ሰውን በቀጥታ ሊያጠቃ የሚችል ቫይረስ የለም ብለው ቻይና ይህን ጉዳይ በተደጋጋሚ ማብራሪያ ሰጥታበታለች፤ የዓለም የጤና ድርጅቱን የቀጣይ ጥናት ዕቅድ አንቀበልም ብለዋል።