ቻይና የመከላከያ ሚኒስትሯን ከሥልጣን አነሣች

ፎቶ ፋይል፡ የመከላከያ ሚኒስትር እና የክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት ጀኔራል ሊ ሻንግፉ

ቻይና፣ የመከላከያ ሚኒስትሯን ከሥልጣን አባረረች። ሚኒስትሩ፣ በሦስት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ከሓላፊነት የተነሡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ናቸው፡፡ የቻይና ውሳኔ፣ በፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የአመራር ቡድን ውስጥ መረጋጋት ስለመኖሩ ጥያቄ አሥነስቷል።

የመከላከያ ሚኒስትር እና የክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት ጀኔራል ሊ ሻንግፉ፣ ለሁለት ወራት ከሕዝብ እይታ ርቀው ከቆዩ በኋላ፣ በዛሬው ዕለት ከሥልጣን እንደተባረሩ፣ የመንግሥቱ ብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል። ባለፈው ሐምሌ ወር፣ ከሥልጣን የተነሡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ’ም የክልል ምክር ቤት አባልነትም እንደተሰረዘ አስታውቃለች።

ከፍተኛው የአገሪቱ ሕዝባዊ ሸንጎ ቋሚ ኮሚቴ፣ የሚኒስትሩን መባረር አስመልክቶ ምንም ዐይነት ማብራሪያ ባይሰጥም፣ የሁለቱን ሰዎች ከሥልጣን የመነሣት ውሳኔ ግን እንዳጸደቀው፣ መንግሥታዊው የዜና ወኪል ሲሲቲቪ ዘግቧል።

ቤጂንግ፣ ከፊታችን ጥቅምት 18 እስከ 21 ቀን በሚካሔደው የመከላከያ ባለሥልጣናት መድረክ የሚሳተፉ እንግዶቿን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ ሊን የሚተካ ባለሥልጣን እስኪሠየም ድረስ፣ አገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ሳይኖራት ትቆያለች።

የ65 ዓመቱ ሊ፣ ለመጨረሻ ጊዜ በአደባባይ የታዩት፣ በነሐሴ ወር መገባደጃ ላይ ነው፡፡ ሮይተርስ ባለፈው ወር እንደዘገበው፣ ሊ፣ በመሣሪያ ግዥ ወቅት ተፈጽሟል በተባለ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በምርመራ ላይ ነበሩ።

ጀኔራል ሊ ሻንግፉ፣ አገራቸው ቻይና፣ የውጊያ አውሮፕላኖችን ከሩስያ በመግዛቷ የተነሳ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሺ፣ ለሦስተኛ ጊዜ የአገሪቱን የመሪነት ሥልጣን ከጀመሩበት ካለፈው መጋቢት ወር አንስቶ የተሰየሙና ለአጭር ጊዜ ያገለገሉ የቻይና መከላከያ ሚኒስትር ኾነዋል።